“የሳይበር ደኅንነት ጥናት እና ምርምሮች ከሀገር አቀፍ አልፈው ቀጠናዊ እና አህጉራዊ እንዲኾኑ እንሠራለን”

44

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር

አዲስ አበባ: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ 4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በዚህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር
ባዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደም ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ የሚደረጉ ኮንፈረንሶች በተቋማት መካከል የዕውቀት ሽግግርን በመፍጠር የዘርፉን ተመራማሪዎች ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላል ብለዋል። ተመራማሪዎች የሠሯቸውን ሥራዎች እንዲኹም የፈጠሩትን ዕውቀት የሚያጋሩበት አስፈላጊ መድረክ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ሀገራት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያሥመዘገቡ በሥልጣኔ ጎዳና ለመገስገስ ያበቃቸው ዋነኛ ምክንያት ለቴክኖሎጂ ጥናት እና ምርምር የሠጡት ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

አሁን ባለንበት የመረጃ ዘመን እያንዳንዱ መረጃ ከየትኛውም ሃብት በላይ የሀገራት የመወዳደሪያ አቅም መኾን ችሏል ሲሉም ተናግረዋል። በዘመኑ የመወዳደሪያ አቅም ላይ የበላይነት ለመያዝ ደግሞ ወሳኙ ጉደይ በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ “በቀጣይ የሚካሄዱ የሳይበር ደኅንነት ጥናት እና ምርምሮች ከሀገር አቀፍ አልፈው ቀጠናዊ እና አህጉራዊ እንዲኾኑ እና የተለያዩ አካላት የሚሳቸፉባቸው እንዲኾኑ እንሠራለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን የመቄዶንያ የአረጋውያን ማዕከልን ጎበኙ
Next articleዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ለሚያደርገው ጥረት ከተቋማት ጋር በትብብር መሥራት አሥፈላጊ መኾኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።