“የዩኒቨርሲቲ መማር ማስተማር ፍጹም ሰላምን ይሻል” የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር)

81

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ገና አልተቀበሉም፡፡ ተማሪዎችን በወቅቱ እንዳይቀበሉ ደግሞ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ኾኗል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉባቸው ከተሞች ሰላማዊ ቢኾኑ እንኳን ተማሪዎች የሚመጡባቸው መንገዶች አስተማማኝ አለመኾን ተማሪዎችን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡

ተማሪዎችን በወቅቱ አለመቀበል ደግሞ የመማር ማስተማር ሥራውን ያዛባዋል፡፡ በትምህርት ጥራት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) የመጀመሪያው ሩብ ዓመት መደበኛ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የዝግጅት ሥራ የሚከናወንበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የዝግጅት ሥራ በሚሠራበት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሙሉ ዝግጅት ለማድረግ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ግብዓት ለማቅረብ ማስቸገሩንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተወሰነ ዝግጅት አድርጓል፣ ሙሉ ዝግጅት ግን ማድረግ አልቻለም ብለዋል፡፡ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የግዥ ሠራተኞች እና የተቋሙ መሪዎች ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት እንዳልቻሉም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ዝግጅት ለማድረግ አስቻይ ኹኔታ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው ኹኔታ ተማሪዎችን መቀበል ተማሪዎችን፣ ወላጆቻቸውን እና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብን ስጋት ውስጥ የሚከት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ “የዩኒቨርሲቲ መማር ማስተማር ፍጹም ሰላምን ይሻል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ የተሻለ የሰላም ኹኔታ እስከሚፈጠር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መቆዬት እንደሚሻል መግባባታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የሰላም ኹኔታውን ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገሩ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ውሳኔ ለመወሰን እንደተዘጋጁም ነው ያስገነዘቡት፡፡

አቻ ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ማስተማር ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ዩኒቨርሲቲዎች ሥራቸውን እንዲጀምሩ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና የሚሰጡ በመኾናቸው በወቅቱ ገብተው ባለመማራቸው ተማሪዎች ላይ ጫና ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ የሰላም ዋጋ ከፍ ያለ ነው፣ ሰላም እንዲፈጠር ሁሉም አካል የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋልም ብለዋል፡፡

“ተማሪዎችን ለመቀበል የቻልነውን ያህል ዝግጅት እያደረግን ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። ለመቀበል የሚያስችል ኹኔታ ሲኖር ተማሪዎች እንጠራለን፤ ተማሪዎች ባሉበት ኾነው ከአሁን ቀደም የተማሯቸውን እያነበቡ፣ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ በትዕግሥት እንዲጠብቁም ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዩኒቨርሲቲው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቅቋል” የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር)
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን የመቄዶንያ የአረጋውያን ማዕከልን ጎበኙ