“ዩኒቨርሲቲው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቅቋል” የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር)

87

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችልን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቻቸውን ቀደም ብለው አጠናቅቀዋል፡፡ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ተማሪዎችን ለመቀበል ከሚጠባበቁ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አንደኛው ነው፡፡

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ምክንያት የተጓተተውን መማር ማስተማር ለማካካስ መስከረም/2016 ዓ.ም መጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ተማሪዎችን ለመቀበል አስቀድሞ አቅዶ እንደነበርም ተመላክቷል፡፡

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት የተጓተተውን እና የተዛባውን የመማር ማስተማር ሥርዓት ለማስተካከል ተመራቂ ተማሪዎችን ከመስከረም 3/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለመጥራት በእቅድ ተይዞ ነበር ነው ያሉት፡፡

የምግብ ግብዓት እና ሌሎች ዝግጅቶችን ነሐሴ/2015 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ማጠናቀቃቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ዓመቱን ሙሉ የማይከዘኑ የምግብ ግብዓቶች በመኖራቸው የምግብ ግብዓት በተከታታይ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎችን ለመቀበል በጉጉት እየጠበቁ ባለበት ኹኔታ የጸጥታ ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡ የመብራት ኀይል አስተማማኝ አለመኾን ለአካባቢው ፈተና መኾኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ነዳጅ ላይ ጥገኛ ነው፣ መንገድ ከተዘጋጋ እና የነዳጅ አቅርቦት ከሌለ እንቸገራለንም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ውኃ ከርቀት የሚመጣ በመኾኑ ነዳጅ ከሌለ በዩኒቨርሲቲው ውኃ እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡ መብራቱ አስተማማኝ ባለመኾኑ ነዳጅ ማቅረብ የሚቻልበት ሰላም መረጋገጥ አለበትም ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሙሉ ዝግጅት አድርጎ መምህራን ዝግጁ ኾነው በግቢ ውስጥ እንዲገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በዝግጅት በኩል የተጓደለ ነገር የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ የጸጥታው ኹኔታ የሚሻሻል ከኾነ በሚል በተስፋ እየጠበቁ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን ደኅንነት መጠበቅ ስለሚገባ የተሻለ ጊዜ መምረጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የተሻለ የሰላም ኹኔታ ሲፈጠር ተማሪዎችን እንቀበላለንም ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያስተማረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አበረታች የሰላም ኹኔታ ሲኖር በአስቸኳይ ተማሪዎችን እንደሚጠሩም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከቡና የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን
Next article“የዩኒቨርሲቲ መማር ማስተማር ፍጹም ሰላምን ይሻል” የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር)