
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣይ ሁለት ዓመታት ከቡና የሚገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው ሲል የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሕለማርያም ገብረመድኅን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት ጥራት በተሻለ መልኩ በማቅረብ እና ንግዱን ወደ ተለያዩ ሀገራት በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው።
ባለፈው በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ዐረብ ኢምሬትስ በመላክ አንድ ነጥብ 34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 350 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ከቡና የወጪ ንግድ የሚያገኘውን ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ እየሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ገቢውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ማለትም የቡና ግብይት፣ ጥራት፣ ብክነት እና በጣዕም ደረጃ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቡና ምርትን ጥራት በመጠበቅ እና በማሻሻል ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ዶላር ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ የመስጠት ሥራ ስለመሠራቱም አንስተዋል።
አብዛኞቹ የቡና ዛፎች ያረጁ በመኾናቸው ምርት እና የምርት ጥራታቸው ቀንሷል ብለዋል።
አቶ ሳሕለማሪያም እስካሁን ወደ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኙ የቡና ዛፎች ተጎንድለዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የቡና ምርትን በብዛት እና በጥራት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅርበት እየተሠራ ከመኾኑም በተጨማሪ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ከወጪ የቡና ንግድ ለማግኘት የታቀደውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሳካት በግብይቱ የሚታዩ ተግዳሮቶችን የመፍታት ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ ነው ሲሉም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!