
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የሀገር ግንባታ መሠረታዊያን” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ሚስቴር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ገና አልተጠናቀቀም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
በዚህች ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ውስጥ ሀገረ መንግሥት በአንዴ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ አይደለም ነው ያሉት።
ሁሌም “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” በሚል በየዘመናቱ የሚነሳ ሀሳብ ልክ አይደለም የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ሀገር በአዲስ ሀሳብ ይነቃቃል እንጂ እንደ አዲስ የሚጀመር ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡ በግንባታ ሒደቱ ትውልድን የመቅረጽ ሥራ የዚህ አካል እንደኾነም አስረድተዋል።
ሀገር እንገንባ ሲባልም በአዕምሯችን ውስጥ የሚመጣ የተሻለ ሀገር መገንባት ነው ብለዋል፡፡ ሁሉንም የሚያስተሳስር እና አንድ የሚያደርግ የመግባቢያ መሠረተ ሀሳብ እና ብሔራዊ እሴት እንደሚያስፈልጉም ነው ያስገነዘቡት።
ሀገረ መንግሥት ተገነባ የሚባለው መግባባት የሚያስችሉ ያጋራ መሰረቶች ሲኖሩ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ “በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የጋራ እሴት እና ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ሁነት መፍጠር ትልቅ ሥራ ነውም” ብለዋል
በዚህ ሀገር ውስጥ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ የሚገልጹት ሚኒስትሩ፤ ከሀሳብ እስከ ብሔር፤ ከጾታ እስከ ቋንቋ፤ ከሃይማኖት እስከ እሳቤ፤ በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል ሁነትን መፍጠር መቻል በሀገረ መንግሥት ሥራ ውስጥ ትልቅ ሚና አለው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!