
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
“መልካም” የተባለውን የማሽላ ዝርያ ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ እና የዘር ብዜት ሥራ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ገልጿል። ማዕከሉ የተለያዩ የተሻሻሉ አሠራሮችን ማፍለቅ ወይም ማላመድ፣ የተላመዱ ዝርያዎችን ደግሞ ማባዛት እና ለማኅበረሰቡ ማስተዋወቅ ተቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ የተሻሻሉ አሠራሮችን በማላመድ ወደ አርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ገልጿል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ “መልካም” የተባለው የማሽላ ዝርያ አንዱ ነው።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ምንተስኖት ወርቁ እንዳሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት የማሽላ ዝርያውን ከማላመድ ባለፈ ወደ አርሶ አደሩ የማስተዋወቅ እና የዘር ብዜት ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።
በ2015/16 የምርት ዘመን በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በ11 ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት ሥራ እየተሠራ መኾኑን በማሳያነት አንስተዋል። የዘር ብዜቱ ለ2016/17 የምርት ዘመን ለአምራች ማኅበራት፣ ለምርጥ ዘር ድርጅቶች፣ ለምርምር ማዕከላት እና ለዩኒቨርሲቲዎች የሚሰራጭ ነው።
ዝርያው በምዕራብ ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር በለሳ እና ጠገዴ ወረዳዎች እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ቆላማ አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ እይገኛል ተብሏል።
በሞቃታማ አካባቢዎች የሚመረት፣ ለምግብ እና ሌሎች አገልግሎት የሚውል እና በሦስት ወራት የሚደርስ መኾኑ ከአካባቢው ዝርያ የተለየ ያደርገዋል። ዝርያው በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል። ድርቅን የሚቋቋም እና በአጭር ጊዜ የሚደርስ በመኾኑ በዝናብ አጠር አካባቢዎች ተመራጭ አድርጎታል።
በ2014/15 የምርት ዘመን በበለሳ አካባቢ 170 ሄክታር መሬት ላይ በዝርያው ተሸፍኖ ነበር።
የምርምር ማዕከሉ ከመልካም ማሽላ በተጨማሪ 1 ሺህ 400 ኩንታል የስንዴ፣ የሽምብራ፣ የባቄላ፣ የጤፍ እና የሌሎች ሰብሎችን ዘር ለአርሶ አደሮች እና ለዘር አባዥ ማኅበራት ማሰራጨቱን አንስተዋል።
የጎንደር ምርምር ማዕከል ሥራ ከጀመረበት ከሐምሌ 1/1996 ጀምሮ በርካታ የተለያዩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማላመድ ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከማዕከላዊ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜን ጎንደር ዞኖች እስከ ሁመራ አካባቢ ተደራሽ አድርጎ አየሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!