
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ አጠናቀው ተማሪዎችን እየተቀበሉ ነው፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ዝግጅታቸውን አጠናቀው የተማሪዎችን መምጫ ጊዜ የሚጠባበቁ ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ፡፡ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ተማሪዎችን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንደኛው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው የዝግጅት ምዕራፉን በክረምት ወቅት ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ እንደማንኛውም ጊዜ በ2016 ዓ.ም የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ተማሪዎች የሚጠሩበትን ጊዜ ወስኖ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው የቅድመ ምረቃ እና የድሕረ ምረቃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር አቅዶት ከነበረው ጊዜ መዘግየቱንም ገልጸዋል፡፡
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ከጀመረ ጀምሮ ለድሕረ ምረቃ ተማሪዎች ትምህርት እየሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የዝግጅት መዕራፋቸውን ቀደም ብለው መጨረሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለተማሪዎች የተሻለ ጊዜ እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በላቀ መልኩ በተማሪዎች ተመራጭ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በተማሪዎች ፍላጎት መመረጡ ደስተኛ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡ እውቀትን እና በቅቶ መውጣትን የሚሹ ተማሪዎች ዘንድሮም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ሊመርጡ እንደሚችሉ ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ መኾኑን ተማሪዎች ማወቅ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይገጥም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የግብዓት አቅርቦት ቀጣይነት ያለው በመኾኑ የሰላም እጦት ካለ ችግር ሊፈጥር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ “ተማሪዎችን ለመቀበል ከዝግጅት የሚጎድለን የለም፤ ዩኒቨርሲቲው ዝግጅቱን ጨርሶ ተማሪዎችን ለመቀበል እየጠበቀ ነው” ብለዋል፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ተማሪዎች መምጣት እንዲችሉ ሁኔታዎችን መፍቀድ አለብን ያሉት ፕሬዚዳንቱ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ኾነው እየጠበቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የድሕረ ምረቃ ትምህርቱ እየቀጠለ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማርም በሁሉም በኩል ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጀምሮ የትምህርት መጓተት ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ እንደ ሀገር የኮሮና ቫይረስን ጊዜ ያለፍንበት መንገድ እንደተሞክሮ ሊወሰድ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ የተፈጠረውን የትምህርት መጓተት ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ማካካስ መቻላቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በሰሜኑ በነበረው ጦርነትም ጫናው ቢለያይም በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ መስተጓጎል ተፍጥሮ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረውን መጓተት ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ማካካሱንም አስታውቀዋል፡፡ የመማር ማስተማሩ መስተጓጎሉ በትምህርት ጥራቱ ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሳያደርስ ማካካሳቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ በ2016 ዓ.ም ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ለመግባት በተዘጋጁበት ወቅት በክልሉ የሰላም ችግር መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ከአሁን በፊት በነበሩ ችግሮች እንዴት መውጣት እንዳለብን ትምህርት ወስደናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ አሁንም ተማሪዎችን በምንቀበልበት ጊዜ የትምህርት ጥራቱን በማይጎዳ መልኩ ለማስኬድ ልምድ እና ዝግጅት አለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!