
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በወቅታዊነት ያጋጠመው የሠላም ችግር እያሥከተለ ያለው ሰብዓዊና ቁሣዊ ውድመት፣ ሀገርን እና ኢንቨስትመንትን እያወደመ ለወደፊቱም በዘርፉ የሚሠማሩ አከላትን እያራቀ እንደኾነ በውይይቱ ተነስቷል።
አገልግሎት እና ፍትሕ ፈልጎ የሚንከራተተው እየተበራከተ መምጣት፤ የሕዝብ ወገንተኝነት አለመኖር እና የተሳሳተ መረጃ ማሠራጨት እንደተበራከተ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ እነዚኽን ችግሮች ለመቅረፍ የመንግሥት ሠራተኛዎች ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡
በውይይቱ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ 71 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ14 ትምህርት ቤቶች ብቻ የተማሪ ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ ከእነዚህ ትምህርት ውስጥ በአንድ ትምህርት ቤት ብቻ ነው ትምህርት የተጀመረ፡፡
በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም መደፍረሥ የጣና ፍሎራ ልማት ተቃጥሏል፡፡ በዚህም ወረዳው በዓመት 12 ሚሊየን ብር ገቢ ማጣቱን እና ሌሎች በሮያሊቲ ክፍያዎች ይገኙ የነበሩ ገቢዎች መቆማቸው ለአብነት ተነስቷል፡፡
ተወያዮች መንግሥት በሚናገረው ልክ ወደ ተግባር በመቀየር በኩል ውሥንነት እንዳለበት አንሥተዋል፡፡ በደል ደርሶባቸው ለግጭት የተዳረጉ አካላት ቢኖሩም ለዝርፊያ ግጭት የሚቀሰቅሱም እንዳሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተነሱ የአማራ ሕዝብ ችግሮች እና ጥያቄዎች ሳይፈቱ እና ሳይመለሱ ዓመታትን ማለፋቸውን በተወያዮቹ ተጠቁሟል፡፡
በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሠራ ኀላፊዎችም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመመካከር ችግሩን በመፍታት የሕዝቡን ጥያቄ ሊመልሱ ይገባል ነው የተባለው፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ወርቁ ችግሮችን ለመፍታት የውይይትን አሥፈላጊነት እና ችግር ፈቺነት ጠቁመዋል፡፡ “በባሕር ዳር ዙሪያ ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት ሕዝቡን እፎይታ መሥጠት አለብን” ብለዋል፡፡ አቶ በቀለ በቢሊየን ብር በጀት ተመድቦ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ሥራ ማቆማቸውንም ነው ያመላከቱት፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳኛቸው ፈንታሁን በበኩላቸው በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ክልሉ በአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተዳደር መኾኑን ጠቅሰው “በክልሉ ሰላም በዘላቂነት እንዲሠፍን የታጠቁ ሁሉ ትጥቃቸውን አሥቀምጠው ለውይይት መቅረብ አለባቸው” ብለዋል፡፡
የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት እሱባለው መሠለ የሕዝቡን ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት እየጠየቀ እና እየታገለባቸው ያሉት ጥያቄዎች ቢኖሩም የአገልግሎት አሠጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችም ቀላል እንዳልኾኑ አመላክተዋል፡፡
“የአማራ ህዝብ ችግሮች እና ጥያቄዎች እንዲፈቱ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው“ ያሉት አቶ እሱባለው “ለጥያቄዎቹ መፍትሔ ለመሥጠት በመጀመሪያ ሕግ መከበር አለበት” ብለዋል፡፡ “በግጭት የሚፈታ ችግር የለም” ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላማዊ መንገድ እና ቀስ በቀስ እንደኾነም አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!