
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜን አርማጮሆ ወልቃይት ጠገዴና አካባቢው በጎ አድራጎት ማኅበር ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ጋር በመተባበር “ሰላምን እናወርዳለን ለደከሙት ምርኩዝ እንኾናለን” በሚል መሪ መልእክት በሰላም ዙሪያ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የዞኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፤ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የሁመራ ከተማ ነዋሪዎችም “የሰላም እጦት የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ከአጎራባች ወንድሙ የአርማጭሆ ሕዝብ እንዳይገናኝ ለሦስት አሥርት ዓመታት ሲከለከል መቆየቱን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች አሁን ላይ በአንድነት በመገናኘት ሰለ ሰላም መምከር በመቻላችን ደስተኛ ነን ብለዋል።
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት መኾኑን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ከግጭት ይልቅ ለሰላም ዘብ በመቆም የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሰላም አማራጭ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች ያሉት በመኾኑ በወቅቱ ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት ሕዝብን ሊያደምጥ ይገባል ብለዋል።
በመንግሥት መዋቅር ሥር ያሉ የሥራ ኀላፊዎችም የሕዝቡን የልማት ጥያቄ በመመለስና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሰሜን አርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው በጎ አድራጎት ማኅበር የተለያዩ በጎ አድራጎቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ የማኅበሩ ሰብሳቢ ሻለቃ ሙሉቀን አበበ ተናግረዋል።
ማኅበሩ ከበጎ አድራጎት ተግባራት ባሻገር የአካባቢ ሰላምን ለማስጠበቅ በርካታ ተግባራትን እየሠራ መኾኑን የማኅበሩ ሰብሳቢ ጠቁመዋል። የኅብረተሰቡን አንድነት በማጠናከር ባሕል እና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲዘልቅ ማኅበሩ ዓላማ አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከነጻነት ማግሥት የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በማስጠበቅ ነጻነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ አንሥተዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት የአካባቢ ሰላም ሲጠበቅ ነው ያሉት አቶ አሸተ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የሰላምን አማራጭ በመጠቀም የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!