
አዲስ አበባ: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሚኒስቴሩ እንደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ካሉ ተቋማት ጋር በመኾን ነው መተግበሪያዎቹን ያበለጸገው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመተግበሪያዎቹን ይፋዊ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ባካሄደበት መድረክ እንደተነገረው ከዚህ ቀደም 21 የሚኾኑ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ከአጋር ተቋማት ጋር ሲያበለጽግ ቆይቷል።
ዛሬ በይፋ ሥራ እንዲጀምሩ የተደረጉት መተግበሪያዎች በሞባይልና በድረ ገጽ መጠቀም የሚቻልባቸው ሥርዓት ጭምር ናቸው ተብሏል።
መተግበሪያዎቹ “ሉሲ ኢ ኮሜርስ” የተባለ የሀገር ውስጥና የውጭ ምርቶችን ለኦንላይን ግብይት ለማቅረብና ለመገበያየት የሚያገለግል እንደኾነም ተገልጿል፡፡ ጉዞውም ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ በመኾኑ ኢንተርፕራይዞች እንዲገለገሉበት የታሰበ ስለመኾኑም ነው የተብራራው።
ሌላኛው ደግሞ “ሲኦሲ” የተሰኘው የብቃት መመዘኛ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የብቃት ማረጋገጫ ምዘናውን የሚወስዱ ተፈታኞች ከወረቀት ንክኪ በፀዳ መልኩ ምዝገባ ማድረግና ፈተና መውሰድ የሚችሉበት መተግበሪያና ሥርዓት ነው።
3ኛው ደግሞ “ቢኩ” የተሰኘ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ሲኾን ለሥራ ፈላጊዎችም ኾነ ቀጣሪዎች በየአካባቢያቸው ኦንላይን ተመዝግበው የሚያመለክቱበትና የሚቀጥሩበት ሥርዓት ነው። በዚህ ሥርዓት እንደ ሀገር ያለው የሥራ ፈላጊዎችና ቀጣሪዎች እንዲሁም የተፈጠረው የሥራ ዕድል የተሟላ ሀገራዊ መረጃ የሚያዝበትና የሚታወቅበት ነው።
ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል መተግበሪያዎቹን ያለሙትን ወጣቶች ፣ ያስተባበሩትን ተቋማት እና ግለሰቦችን ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሠግናችኋለች ብለዋል።
የለሙት መተግበሪያዎችና ሥርዓቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ዓለሙን የመቀላቀልና ሀገራዊ ልማቶች ዳር የማድረስ ሚና አላቸው ነው ያሉት።
የሕዝብ ችግር ፈቺና ኑሮን አቅላይ የመረጃ ሥርዓቱንም የሚያግዝ እንደኾነ ተናግረዋል።
መተግበሪያዎቹን ሚኒስትሯ እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያው ሥነ ሥርዓት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!