
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኦስትሪያው ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ከ30 ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘው ሬድ ቡል አሬና ስታዲየሙ ከኢንተር ሚላን ጋር ይጫወታል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በምድብ አራት የተደለደሉ ሲኾን፤ ኢንተር ሚላን በሰባት ነጥብ እና በሁለት የግብ ልዩነት በሁለተኛነት ተቀምጧል፡፡
ሳልዝበርግ ደግሞ በሦስት ነጥብ እና በአንድ ግብ እዳ ሦስተኛ ነው፡፡ ቤንፊካ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡
ምድብ አራትን ሪያል ሶሲዳድ በሰባት ነጥብ እና በሦስት የግብ ልዩነት በመምራት ላይ ነው፡፡ታዲያ ኢንተር ሚላን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ በእጅጉ ይጠቅመዋል፡፡
የሳልዝበርጉ አሰልጣኝ ገርሃርድ ስትሩበር በጨዋታው አማካዩ ማውሪስ ክጃርጋርድ በትከሻ ጉዳት ከሜዳ እንደሚርቅ ጠቁመዋል፡፡ ተከላካዮቹ አሌክሳ ቴርዚች እና ካሚል ፒያትኮውስኪ በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፉም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ሬድ ቡል ሳልዝበርግ የኦስትሪያን ቡንደስሊጋ በ29 ነጥብ እየመራ የሚገኝ ቡድን ነው፡፡
የኢንተር ሚላኑ አሰልጣኝ ሲሞን “እኛ በሻምፒዮንስ ሊጉ ጠንካራ አቋም እያሳየን እንገኛለን፤ ይህን ጥንካሬያችንን አስቀጥለን በድል ጎዳና እንጓዛለን፤ ዛሬም በማሸነፍ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩን ወደ ቀጣዩ ዙር እንድናልፍ እንጫወታለን” ብለዋል፡፡
ኢንተር ሚላን በሴሪኤው 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን በመርታት እና በአንዱ ብቻ በመሸነፍ በ28 ነጥብ በፊት አውራሪነት ይገኛል፡፡ ስለኾነም የዛሬው ጨዋታ ይቀለዋል ሲል ዩሮ ስፖርት ዘግቧል፡፡
በሲሞን ኢንዛጊ የሚሰለጥነው ኢንተር ሚላን ባለፈው የውድድር ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ደርሶ መሸነፉ አይዘነጋም፡፡
በሌላ ጨዋታ ናፖሊ በስታዲዮ ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና ስቴዴየም ከጀርመኑ ዩኒየን በርሊን ጋር ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ይጫወታል፡፡ በምድብ ሦስት የተደለደለው ናፖሊ በሦስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ እና ሪያል ማድሪድ ከተሸነፈ ምድቡን የግብ ብልጫ ያለው ቡድን ይመረዋል ሲል ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
ተጋጣሚው ዩኒየን በርሊን ሦስት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በሦስት የግብ እዳም ያለምንም ነጥብ በደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጧል፡፡
ዩኒየን በቡንደስሊጋው በ10 ጨዋታዎች በስምንቱ ተሸንፎ እና በሁለቱ አሸንፎ በስድስት ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተቀምጧል፡፡
በአንጻሩ ናፖሊ በሴሪአው 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን በመርታት፣ በሁለቱ በመሸነፍ እና በሦስቱ አቻ ወጥቶ በ21 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ዩኒየን በርሊን በቡንደስሊጋው በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን ያለፉት 12 ጨዋታዎች ተሸንፏል፣ ይህ ማለት ግን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ሲ በናፖሊ ይሸነፋል ማለት ባይኾንም ክለቡ ወደ ጥሎ ማለፍ ደረጃዎች የመድረስ ተስፋው በክር የተንጠለጠለ እንደኾነ ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሲያ “ጨዋታው ቀላል አይደለም፤ የምንገጥመው በአውሮፓ ውስጥ ካሉት ክለቦች አንዱን ነው፤ የምንጫወተውም ለማሸነፍ ነው” ብለዋል።
የዩኒየን አሰልጣኝ ፊሸር “የቡድኑ ስብስብ ጥሩ አይደለም፤ በእርግጥ የምንጫወተው ለማሸነፍ ነው፤ ውጤት እንደምናገኝ ተስፋ አድርገን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው” ብለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!