
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።
አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ወረዳው እና ከተማ አሥተዳደሩ በጋራ በመኾን ለሚሊሻ እና ለሰላም አስከባሪ አባላት ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሥልጠና ተሰቷል፡፡
በሚያገኙት ሥልጠና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመኾን ሰላም ለማስከበር እንደሚሠሩ የሚሊሻ አባላት ተናግረዋል።
ባለፉት ወራት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥፋቶች አስከትሎ እንደነበር ያነሱት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ ሻንበል ጋሻው ንጉሤ ከሕግ እና ሥርዓት ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ ኪሳራው የከፋ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በወረዳው እና አካባቢው ለሚገኙ የሚኒሻ እና ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ተከታታይነት ያለው ሥልጠና በመስጠት የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠራምሩ አሥተዳዳሪው አክለዋል፡፡ የመልሶ ማደራጀት ሥራ በቀጣይ እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የዞኑ ሚሊሻ የሰው ኀይል አደረጃጀት ፀጥታ ስምሪት ቡድን መሪ ሰለሞን አለባቸው በወረዳው እና በከተማ አሥተዳደሩ አሁን ላይ የሚታየውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅቶ በመሥራት ሰላምን ለማስፈን ያለመ ውይይት እንደተደረገ አስረድተዋል፡፡
መንገድ በመዘጋቱ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ተስተጓጉለው እንደቆዩ ያስታወሱት አቶ ሰሎሞን በዳባት ወረዳ እና ዙሪያው በተወሰኑ ቀበሌዎች የተቋረጠውን የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት ለመመለስ የጸጥታ መዋቅሩ ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
ከ450 በላይ ሚሊሻዎች እና ሰላም አስከባሪዎች ሥልጠናውን እንደወሰዱ የተገለጸ ሲኾን በቀጣይም ሕግ የማስከበር ሥራውን በቁርጠኝነት የጸጥታ መዋቅሩ እንደሚሠራ ተናግረዋል ሲል የዳባት ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!