
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአመለካከት እና የተግባር አንድነትን አስጠብቆ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን መኾን የሚተጋ ጠንካራ የመንግሥት መሪዎችን መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
በሁሉም የኀላፊነት እርከን ላይ ለሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የሚሰጠው ሥልጠና ተጠናክሮ ቀጥሏል። በመጭዎቹ ቀናትም ከ21 ሺህ 800 በላይ አመራሮች ወደ ስልጠና ይገባል ብለዋል።
ፓርቲው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ ተመርጦ መንግሥት በመመስረት የተቀበለውን ኀላፊነት ለመወጣት የአመራሩን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች አፈጻጸም በመገምገም ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን መለየቱን ጠቁመው፤ እንደ ክፍተት የታዩትን ለመሙላት እና አመራሩ በቀጣይ ውጤታማ እንዲሆን የፍላጎት ዳሰሳ ተደርጎ ስልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አመራሩ ለተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታዎች እንዲዘጋጅ፣ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በብቃት እንዲወጣ የአቅም ግንባታ ስልጠናው ማስፈለጉንም ነው የተናገሩት።
የስልጠናው ዓላማ አመራሩን በእውቀት ማበልጸግ፣ የአገልጋይነት መንፈስና አስተሳሰብ እንዲላበስ ማድረግ እና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ የሚያግዝ ክህሎትን ማጎልበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዚህም “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዙ አጀንዳዎች መቀረጻቸውን ነው ያስረዱት።
እስካሁን በሁለት ዙር በተሰጡ የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ከ13 ሺህ 500 በላይ አመራር መሰልጠኑን ጠቅሰው፤ ከጥቅምት 30/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከ21 ሺህ 800 በላይ የ3ኛ ዙር ሰልጣኞች ወደ ስልጠና እንደሚገቡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአመለካከት አንድነት በእቅዶች፣ በዓላማዎች እና በመርሆዎች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር መሆኑን ያነሱት አቶ አደም የተግባር አንድነት ደግሞ የተያዙ እቅዶችን በተቀራራቢ መንገድ እንዲፈጸሙ ማድረግ ነው ብለዋል።
ሥልጠናው የመሪዎችን አቅም በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እና የሀገር ግንባታ ጉዞን የሚያሳካ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር ያስችላል ነው ያሉት።
አመራሩም በሀገር እና ትውልድ ላይ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ማስቀረት እና የትናንት ወረትን ወደ ዛሬና ነገ ምንዳ የማሸጋገር ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለበትም አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!