
አዲስ አበባ: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የዳታ ሴንተር አገልግሎት በመስጠት ሀገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን ወጭ መቀነስ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ ከአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን እና ከዊንጉ አፍሪካ ጋር በመቀናጀት ለግሉ የፋይናንስ ዘርፎች አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈጣን የዳታ ሴንተር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ውይይት እያካሄዱ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ለምትገነባው ዲጂታል ኢኮኖሚ በፍይናንስ ዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ወጪ ቆጣቢ የዳታ ሥርዓት ሴንተርን መጠቀም አለባቸው ብለዋል።
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሄኖክ አሕመድ እንደ ሀገር በዳታ ሴንተር ሥርዓት ኢንቨስት የሚያደርጉ ድርጅቶችን ለመሳብና በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የዊንጉ አፍሪካ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተሾመ ወርቁ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረ 1 ዓመት ከ6 ወር ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡
ድርጅታቸው በተለይም ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የዳታ ሴንተር አገልግሎትን ለፋይናንስ ተቋማት በመስጠት ሥራቸውን ለማቅለል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!