
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስቀድመው መጥራት አልቻሉም፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን መጥራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ለተማሪዎቻቸው የደኅንነት ዋስትና እስኪሰጥ ድረስ ከመጥራት ተቆጥበዋል፡፡
በክልሉ የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን እያስተማሩ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ተዛብቶበት እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ሦስት ወሰነ ትምህርቶችን ለማስተማር አቅደው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ የተጓተተውን ትምህርት ለማካካስ አስቀድመው በመጥራት ትምህርት ለመጀመር አቅደው እንደነበር አንስተዋል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በእቅዳቸው መሠረት ተማሪዎችን መቀበል አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎችን ከመስከረም 11/2016 ዓ.ም ጀምረው ጠርተው እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተማሪዎችን የመቀበያ ጊዜ ማራዘማቸውንም ተናግረዋል፡፡ በቅርብ የተደረገ ጥሪ አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመምጣት የሚያስችል መንገድ እንደማያገኙ በመረዳት እና ተማሪዎቹም ለመምጣት እንደሚቸገሩ ባስታወቁት መሠረት ጥሪውን ማራዘማቸውን ነው የገለጹት፡፡
በጸጥታው ምክንያት በተፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ተማሪዎችን ለመጥራትም ኾነ የግብዓት አቅርቦት ለማግኘት ፈተና ኾኖባቸው እንደቆየም አስታውሰዋል፡፡ የግብዓት አቅራቢ ነጋዴዎች ግብዓት ለማግኘት ሲቸገሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም የጤፍ ግብዓት ፈትኗቸው እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ለገጠማቸው ችግር መፍትሔዎችን በመውሰድ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን እያስተማረ መኾኑንም ገልጸዋል፤ ሌሎች ችግሮች ተፈጥረው መደናቀፍ ካልተፈጠረ በስተቀር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነንም ብለዋል፡፡
የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ከሆነ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዩኒቨርሲቲው ሁሉንም አይነት ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡ “ተማሪዎች በጉዞም ላይ ሆነ ከገቡ በኋላ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥም የሚመለከተው አካል እውቅና እስከሚሰጥ ድረስ እየጠበቅን ነውም” ብለዋል፡፡ የጸጥታ ሁኔታውን የሚመራው አካል እውቅና የሚሰጥ ከሆነ ተማሪዎችን እንቀበላለን ነው ያሉት፡፡
የሰላም ሁኔታው አስተማማኝ ባለመሆኑ የዓመቱን የምግብ ግብዓት በአንድ ጊዜ ማስገባት እንደማያስችልም አንስተዋል፡፡ የገበያ መስመሩ እስካልተደነቃቀፈ ድረስ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከሰሞኑ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን አይቀበሉም በሚል የተሰራጨው መረጃ ተማሪዎችን ማስደንገጡን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን የማስተማር ፍላጎት እና በቂ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን ሊያውቁት ይገባልም ብለዋል፡፡
የመቅደላ አምባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ካሳ ሻውል (ዶ.ር) መቅደላ አምባ ዪኒቨርሲቲ ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመስከረም 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማዘጋጀት ያለበትን ሁሉ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የጸጥታ ችግር ካልኾነ በስተቀር እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስቸግር ነገር የለምም ብለዋል፡፡ የሰላም ሁኔታው ከተስተካከለ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ይቀበላል ነው ያሉት፡፡ ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይፈጠር አስቀድመው ሰርተው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ “የጸጥታ ሁኔታውን አስተማማኝነት ማረጋገጫ ካገኘን ተማሪዎችን ለመጥራት የሚያስቸግረን ነገር የለምም” ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አይቀበሉም የሚለውን ሀሰተኛ መረጃ በመተው ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ የሰላሙ ሁኔታ መስተካከል ካሳየ ተቀብለው እንደሚያስተምሯቸው በመረዳት ዝግጅት እያደረጉ እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!