
ሰቆጣ: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በኮረም ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በኩታገጠም የተዘራ የጤፍ ሰብል ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱ ተሞክሯቸውን ያካፈሉት አርሶ አደር ንጉሴ መለሰ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት ከሚያገኙት ምርት በእጥፍ ምርት እንደሚያገኙ ገልጸው ጤፍን በኩታገጠም በመዝራታቸው በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ ይገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አርሶ አደር ተስፋ ቀለታ በበኩላቸው የኩታገጠም ሰብል የአርሶ አደሮችን መተባበር እና መተጋገዝን ከማጠናከሩም ባሻገር ተመሳሳይ ምርት እንድናገኝ የሚያደርግ ተሞክሮ ነው ብለዋል።
የኮረም ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አዳነ ጫረው እንደገለጹት በኮረም ከተማ በተያዘው ዓመት 600 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 600 ነጥብ 25 ማሳካታቸውን ገልጸዋል።
በጤፍ ኩታገጠም 136 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲኾን ከዚህም 9 ሺህ 375 ኩንታል ምርት ለማግኘት እንዳቀዱ አብራርተዋል።
አቶ አዳነ ጫረው እንደገለጹት አርሶ አደሮች በኩታገጠም መዝራታቸው ለግብርና ድጋፍ እና ክትትል ምቹ ከመኾኑም ባሻገር ምርታማነቱም አስተማማኝ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሮችም በተለመደው የመተባበር ሥራ የደረሰውን ሰብል በመሰብሰብ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያደርሰው ጉዳት እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
በጉብኝቱ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የኮረም ከተማ አሥተዳደር ከንቲቫ፣ የሥራ ኀላፊዎች እና ሞዴል አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!