
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮነን በዞኑ በተከሰተ የኮሌራ በሽታ እስካሁን 300 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በበሽታው የተጠቁት በ25 የጤና ተቋማት ተኝተው ሕክምና እየተደረገላቸው መኾኑንም ኀላፊዋ ገልጸዋል። የኮሌራ በሽታ ታካሚዎችን ለማከም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በክልሉ አማካኝነት እየቀረቡ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም ወደ ጤና ተቋማቱ እንደሚሠራጩ አንስተዋል፡፡
የኮሌራ በሽታን በጤና ተቋም ብቻ በማከም መከላከል እንደማይቻል የገለጹት ሲስተር ፈለቁ የበርካታ ተቋማትን እና አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅም አስረድተዋል፡፡
የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አዲሴ ሰይድ የኮሌራ በሽታ የተገኘባቸውን ሰዎች በመለየትና ድንኳን በማዘጋጀት የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ችግሮችን ያሳለፈ በመኾኑ የኮሌራ በሽታ ታካሚዎች ቁጥር የሚጨምር ከኾነ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም አስረድተዋል ሲል የዘገበው የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!