
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሲቪክ ማኅበራትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ተገልጿል። ሲቪክ ማኅበራት ከመንግሥት ነጻ የኾኑ፣ በራሳቸው የሚተዳደሩ እና አትራፊ ያልኾኑ በጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች እንደኾኑ ይታወቃል። ዋና ሚናቸው ደግሞ መንግሥት የሥልጣን ገደቡን እንዳያልፍ መከታተል ፣ የሥራ ኀላፊዎችን የሙስና አሠራር ማጋለጥ እና ለመልካም አሥተዳደር መታገል ነው። ዜጎች ስለመብት እና ግዴታ ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና መቻቻል ፣ መከባበር ፣ መቀራረብ እና መሰል ዴሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲዳብሩ ይሠራሉ።
የፖለቲካ መሪዎችን ብቃት የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት፣ የምርጫ ሂደትን መከታተል እና መታዘብ የመሳሰሉ ተግባራትን በመፈጸም ለሀገራዊ ሰላም መስፈን እና ለዴሞክራሲ ማደግ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ኢንጅነር አድማሱ ገበየሁ (ዶ.ር) “መግባባት” በሚል በ2010 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ አስቀምጠውታል።
በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በሀገራዊ ልማት ላይ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ ከሚገኙ ሲቪክ ማኅበራት መካከል የመምህራን ማኅበር በቀዳሚነት ይቀመጣል። ማኅበሩ ከተመሠረተበት ከ1940 ዓ.ም ጀምሮ የአባላቱን መብት እና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚናው የጎላ እንደነበር የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ፕሬዚዳንት እና የዓለም አቀፍ መምህራን ቦርድ አባል ዮሃንስ በንቲ (ዶ.ር) ነግረውናል
ማኅበሩ “የመምህራን ኅብረት” በሚል ሥያሜ ነበር የተመሰረተው። ከአንድ ዓመት በኋላ 32 አባላትን በመያዝ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት መተዳዳሪያ ደንብ በማውጣት ወደ ሥራ ገብቷል። እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ ፣ የትምህርት ደረጃን ለማሻሻል እና የአባላቱን መብት እና ጥቅም ለማስከበር ዓላማዎችን መሰረት አድርጎ ነበር የተመሠረተው።
ይሁን እንጅ ከትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ማኅበሩ የአባላቱን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ሀገራዊ ልማት እንዲፋጠን ዓላማ አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል።
ማኅበሩ ከተመሠረተ ጀምሮ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሥፈን ባከናዎናቸው ተግባራት በየጊዜው በነበሩ መንግሥታት ጥርስ ተነክሶበት እንደነበርም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት። በ1953 ዓ.ም በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማኅበሩ በዐፄ ኃይለስላሴ መልካም ዕይታ አልነበረውም። በ1960ዎቹ መጀመሪያ መንግሥት ግልጽ ባልኾነ እና ማኅበሩንም ባገለለ መንገድ የትምህርት ሴክተሩን ክለሳ በማድረጉ ተቃውሞ አስነስቷል። በትምህርት ሴክተሩ ብቻ ሳይኾን በሁሉም ሴክተሮች ላይ ክለሳ እንዲደረግ ተቃውሞ በመነሳቱ ለሥርዓቱ መውደቅ አንድ ምክንያት መኾኑን አንስተዋል። በደርግ ሥርዓትም ሕዝባዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ምርጫ በተካሄደባቸው ጊዜያት ምርጫው ሰላማዊ እንዲኾን እና ጤናማ ውድድር እንዲኖር ትምህርት በመሥጠት እና የምርጫ ሂደቱን በመታዘብ ለዴሞክራሲ መጎልበት ሲሠራ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በ1997 ዓ.ም መንግሥት ምርጫ እንዲያካሂድ ግፊት በማድረጉ ከመንግሥት ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በአጀንዳ ተይዞ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል ብለዋል። የማኅበሩን አባላት በማስተባበር በትላልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ ሲሠራም ቆይቷል።
አሁን ላይም ማኅበሩ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እና የሽግግር ፍትህ ረቂቅ እና አዋጅ ሲዘጋጅ ጀምሮ በነበሩት ውይይቶች እየተሳተፈ ይገኛል። ይህም ማኅበሩ አሁን ካለው በተሻለ ተደማጭ ኾኖ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ መጎልበት እና ልማት መፋጠን የድርሻውን እንዲወጣ አቅም እንዲፈጥር አድርጎታል ነው ያሉት። በቀጣይም አጠቃላይ በሀገሪቱ የሚገኙ ሲቪክ ማኅበራት ሁለንተናዊ ተሳትፏቸው እንዲጠናከር መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥርም ጠይቀዋል።
ማኅበሩ ትምህርት ቤቶች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ እና ሴቶች በሥራ ቦታ የሚደርስባቸውን ጾታዊ ትንኮሳ ለመከላከል ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በኢትዮጵያ ለማስፋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ማኅበሩ አሁን ላይ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ 700 ሺህ አባላትን ይዟል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!