
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚፈጸሙ የከተሞች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጥራት እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ነዉ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስትር ጫልቱ ሳኒ የኢትዮጵያ የከተሞች መሰረተ ልማት ግንባታ በሙያው የካበተ ልምድ ያለው የሰዉ ኀይል እጥረት፣ የጥራት እና የቴክኖሎጂ ችግሮች እንዳሉበት ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር ይህንን ለመፍታት እና በዘርፉ ብቁ የሰዉ ኀይል በማሰማራት ጥራት ያላቸዉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚሠሩ መሰረተ ልማቶችም የዚሁ አካል መኾናቸዉን ጠቅሰዋል።
ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ የገንዘብ እና የክህሎት ድጋፍ እያገኘ መኾኑንም ነዉ ያነሱት።
ይኽ መድረክ በዘርፉ ያለዉን ችግር ለመፍታትና ጥራት ያላቸዉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚያግዝ መኾኑን ነዉ የተናገሩት። ኢትዮጵያ በከተሞች መሰረተ ልማት በ10 ዓመት መሪ እቅድ የምታደርገውን ጉዞ የሚደግፍ ነዉም ብለዋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳሬክተር ኦስማኔ ዲኦን ኢትዮጽያ የከተሞች መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እየሠራች ያለዉ ሥራ የሚመሰገን ነዉ ብለዋል።
በከተሞች የሚሠሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጥራት ያላቸዉ፣ ለማኅበረሰቡም ተገቢዉን አገልግሎት የሚሰጡ መኾን አለባቸዉም ነዉ ያሉት።
በመድረኩ መሰረተ ልማት ለኢኮኖሚዉ ያለዉ ድርሻ፣ ጥራት ያለዉ መሰረተ ልማትን በከተሞች እንዴት ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል እና የኮንስትራክሽን ዘርፉን በምን መልኩ መደገፍ እንደሚገባ ምክክር ይደረግባቸዋልም ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉኡሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!