ከ40 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት በመስኖ ልማት ለማምረት መታቀዱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

43

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የመልማት አቅም እንዳለው የግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በክልሉ በ2016 ዓ.ም 3 መቶ 33 ሺህ 400 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየሠራ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በደቡብ እና በሰሜን ወሎ ዞኖች እና በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመስኖ መሬት የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ደግሞ የመስኖ መሬት ከመለየት ባለፈ ወደ ዘር መግባታቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።

እስከ አሁን ከ48 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት ተለይቷል፤ 10 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ታርሷል፤ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ከፍተኛ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃ ሃብት እንዳለው ያነሱት ኀላፊው ሃብቱን በተገቢው መንገድ ለመጠቀም በየደረጃው የሚገኘው የሥራ ኀላፊ እና ባለሙያ ትኩረት እንዲሠጥ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ አባ መፍቀሬ ሰብእን ፈለኳቸው፤ ፈልጌም አገኘኋቸው”
Next article“በከተሞች የሚሠሩ መሰረተ ልማቶች ጥራት ያላቸዉ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው” የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚንስቴር