
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዓይኔ ናፈቀቻቸው፣ ጀሮዬ ከአንደበታቸው የምትወጣውን ቃል ለመስማት ጓጓችላቸው፣ አስቀድማ አዘነበለችላቸው፣ ከንፈሬ ጉልበታቸውን ለመሳም ቸከለችላቸው፣ እግሬ እሳቸውን ለማግኘት ተጣደፈችላቸው፣ እጄም የቀሚሳቸውን ጫፍ ትነካ ዘንድ ፈለገቻቸው፣ ልቡናዬም በእርሳቸው ቃል ለመመሰጥ ተንሰፈሰፈችላቸው፡፡ እልፎች የሚፈልጓቸውን ፈለኳቸው፣ ፈልጌም አገኘኋቸው፣ እልፎች እጅ የሚነሱላቸውን እጅ ነሳሁላቸው፡፡
እልፎች ጉልበታቸውን ለመሳም፣ ጸሎተ ማርያም ለማስደገም ይጓጉላቸዋል፣ ተራራውን ወጥተው፣ ቆልቁለቱን ወርደው ይፈለጓቸዋል፤ ባገኟቸው ጊዜም ደስ ይሰኙባቸዋል፣ ከእርሳቸው ጋር በረከት አለች፣ ከእርሷቸው ጋር ረድኤት ትኖራለች፣ ከእርሳቸው ጋር ፍቅር ከነግርማዋ ትዋባለች፣ ከእርሳቸው ጋር አምላክ ያከበራት ሰውነት ትገለጣለችና፡፡
ማን አለ? በአንደበታቸው ለዛ ያልተማረከ፣ ማን አለ? በፍቅራቸው ብርታት ያልተንበረከከ፣ ማን አለ? አብዝቶ የማይወዳቸው፣ ማን አለ? አባቴ እያለ የማይጠራቸው፣ ማን አለ? መንገድ ላይ አይቶ የሚያልፋቸው፡፡ ሁሉም ይወዳቸዋል፣ ሁሉም አባቴ ይላቸዋል፣ ሁሉም ያከብራቸዋል፡፡
እርሳቸው ያደረሰው ሁሉ የሚያርፍባቸው የዋርካ ጥላ ናቸው፤ እርሳቸው የሚሻገር ሁሉ የሚያልፍባቸው የዘመን ድልድይ ናቸው፤ እርሳቸው ሁሉ የሚወዳቸው የፍቅር ምልክት ናቸው፤ እርሳቸው ሁሉም አባቴ የሚላቸው የፍቅር እና የመንፈስ ወላጅ ናቸው፤ እርሳቸው ሰውነት የሚገለጥባቸው የሰውነት አርዓያ ናቸው፤ እርሳቸው ፈተና በበዛበት ዘመን ፈተናን ድል የመቱ ገድለኛ ናቸው፤ እርሳቸው የጠወለገች ልብ የምትለመልምባቸው በአንደበታቸው የሚያለመልም ውኃ የሚፈስስባቸው አፍላግ ናቸው፤ እርሳቸው የተራቆተች ምድር ካባ የምትደርብባቸው፣ መጎናጼፊያዋን የምትከናነብባቸው ብርቱ ሠራተኛ ናቸው፤ እርሳቸው የተከዘች ልብ የምትጽናናባቸው፣ ከአንደበታቸው መረጋገትን የሚያወጡ ደገኛ የአምላክ ባርያ ናቸው፡፡
ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በዘውድ እንዳጌጡ፣ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ዙፋን ሳይጨብጡ፣ ኢጣልያ ለዳግም ወረራ ሳትነሳ፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ እጇን ሳታነሳ አስቀድሞ ገና እንደተወለዱ ይነገራል፡፡ በ1920ዎቹ መባቻ ሰሞን የእድሜያቸው መቁጠሪያ ይጀምራል፡፡ በልጅነት ዘመናቸው አጀብ የሚበዛላቸው ነገሥታትን፣ ሰልፍ የሚበዛላቸው መኳንንትን፣ መሳፍንትን፣ የጦር አበጋዞችን፣ የጦር ልብስ ለብሰው በዱር በገደሉ የሚዋደቁ አርበኞችን፣ እንደ ብርቅ የሚታዩ ጳጳሳትን ሲያዩ አድገዋል፡፡ የጳጳሳቱ ቡራኬ ያልተለያቸው፣ የቀሳውስቱ እና የመነኮሳቱ ምርቃት እና በረከት ያልራቀቻቸው ናቸው፡፡
መነሻቸው ቅዱሳኑ ከሚወለዱባት፣ በቅድስና ከሚኖሩባት፣ የቅድስና ተጋደሎ ከሚፈጽሙባት፣ በቅድስናም ከሚያልፉባት፣ በረከት የበዛላቸው ገዳማት እና አድባራት ከመሉባት፣ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ በግርማ ከኖሩባት፣ ልበ ኩሩ ጀግኖች፣ ለሀገር የሚዋደቁ አርበኞች ከሚወለዱባት ከሸዋ ነው፡፡ ሸዋ ተጉለት የእርሳቸው እትብት የተቀበረባት ሥፍራ ናት፡፡ ባሕታዊ አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡ እንዲያው ለስሙ የትውልድ ቀያቸው ተነሳ እንጂ የእርሳቸው ሀገር የትም ነው፣ የእርሳቸው ዘመድ ሁሉም ነው፡፡
ከተጉለት የፈለቁት ደገኛ አባት በዚያው ኖረው፣ በዚያው አላረጁም፣ ይልቅስ እንደ ረጅም ዥረት እየተጓዙ ምድርን አረሰረሷት፣ ፍቅር ዘሩባት፣ ሰላም አፈሰሱባት፣ ሳይደክሙ እና ሳይጠወልጉ አገለገሏት እንጂ፡፡ የስማቸው ትርጓሜ ሰው የሚወደው፣ ሰው ወዳጅ ማለት ነው፡፡ እሳቸው ስለ ስማቸው ሲናገሩ ዋናው ስም የክርስቶስ ስም ነው፤ ሰው ወዳጅ እግኢአብሔር ይባላልና፡፡ በእርሱ ቸርነት ሰው ይወደኝ ነበርና መፍቀሬ ሰብእ ተባልኩ ይላሉ፡፡ ስምን መላእክ ያወጣዋል ይሉት ግብር የተገለጠው ከእርሳቸው እና ከመሰሎቻቸው ላይ ነው፡፡
ታሪኳዊቷ ዙር አምባ ማርያም ደግሞ መፍቀሬ ሰብእ የሚለውን ስም የተቀበሉባት፣ ግብራቸውን እና ስማቸውን አጣምረው መኖርን የጀመሩባት ቅድስት ሥፍራ ናት፡፡ በልጅነት ዘመናቸው እኒያ ለሀገራቸው ከኢጣልያ ጋር ሲዋደቁ የነበሩ አርበኞችን አይተዋል፤ በአርበኞቹ እቅፍ ውስጥም ገብተው ተስመዋል፡፡ “እደግ፣ ተመንደግ፣ ለሀገር የምትጠቅም ያድርግህ” ተብለው ተመርቀዋል፡፡
በልጅነት ዘመኔ ራስ አበበ አረጋይ ሲዋጉ ውለው ከእኛ ቤት አድረዋል፣ አባቴም በሬ አርደው አስተናግደዋቸዋል ይላሉ ያን የልጅነት ዘመናቸውን ሲያስታውሱ፡፡ ራስ አበበ አረጋይ ከጭናቸው አቅፈው ስመዋቸዋል፡፡ ከጭናቸው ላይ አስቀምጠው ምን ልስጥህ ብለው በጠየቁኝ ጊዜ ፈረስ ይስጡኝ አልኳቸው ይላሉ ልብን በሚሰርቀው ፈገግታቸው ያንን ዘመን ወደኋላ እያስታወሱ፡፡
ደገኛው አባት በኢጣልያ ወረራ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት ሲጋዩ፣ ካህናት እና መነኮሳት ሲሰቃዩ፣ ገዳማት ሲፈራርሱ፣ የኢጣልያ ወታደሮች የንጹሐንን ደም በግፍ ሲያፈሱ በልጅነት እድሜያቸው ተመልክተዋል፡፡ በንጹሕ ልባቸው መዝገብም መዝግበው አስቀርተዋል፡፡ ከሸዋ ተጉለት ፊደል ቆጠሩ፣ በለጋ እድሜያቸው በሸዋ አውራጃዎች፣ በተቀደሱ ሥፍራዎች፣ ከቅዱሳን አባቶች ጋር ተመላለሱ፡፡ የልጅነት እድሜያቸው ሳያሰጋቸው፣ ውጣ ውረዱ ሳያደክማቸው፣ የእናት እና የአባት ፍቅር ሳያታልላቸው ሸዋን ወደኋላ ትተው ወደ ቤጌምድር ተሻገሩ፤ በበጌምድርም በአምላክ ፊት የተወደደውን እያደረጉ በየገዳማቱ እና አድባራቱ ተመላለሱ፤ ቀለም የሚነግሯቸው፣ ቃለ እግዚአብሔር የሚያስተምሯቸው አበው አብዝተው ይወዷቸዋል፤ ከእርሳቸው ጋር ተቀምጠው ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰሙ ደቀ መዛሙርትም በፍቅራቸው ይንሰፈሰፉላቸዋል፤ እርሳቸው ለመወደድ የተፈጠሩ፣ በመወደድም የኖሩ ናቸውና፡፡
አታላዩዋን ዓለም ናቋት፤ ፈጽመው ሸሿት፣ ከልቡናቸው አወጧት፤ ከሃሳባቸው አራቋት፤ ዓለም እርሳቸውን በሃሳቧ መያዝ አይቻላትም፤ እርሳቸውን መቅረብ አይሆንላትም፡፡ ለምን ቢሉ ከዓለሙ ሃሳብ ሁሉ በላይ ናቸውና፡፡ በበጌ ምድር መልካሙን ሁሉ አደረጉ፤ አምላክ እየመራቸው፣ በጠብቆቱ እየጠበቃቸው፣ በኃይሉ እያበረታቸው ያኖራቸዋልና፡፡ ከበጌ ምድር ወደ ወሎ ተሻገሩ፤ የተቀደሰው ሥፍራ ቅዱስ ላሊበላ፤ የተቀደሰችው ተራራ ግሸን ደብረ ከርቤ፣ የዋድላ ደላንታ አድባራት፣ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ምኑ ተዘርዝሮ ይዘለቃል፣ እርሳቸው ያልተመላለሱባቸው፣ እርሳቸው ያልደረሱባቸው የወሎ ሥፍዎች ከየት ይገኛሉ?
የሸዋ ሰርጣሰርጦች፣ የበጌምድር ወጣ ገባ ሥፍራዎች፣ የወሎ ተራራ ሸለቆዎች ሁሉ እሳቸው በጸናች ሃይማኖት ተወስነው የተመላለሱባቸው፣ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጹባቸው፣ አጸድ ያስተከሉባቸው፣ ትጉ ጸልዩ፣ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ እያሉ የሰበኩባቸው ናቸው፡፡
የአብያተ ክርስቲያናትን ቅጽር አስውበው ይቀጽራሉ፤ አጸድ ይተክላሉ፤ ዘወትር በሰዎች ልብ ላይ መልካም ዘርን ይዘራሉ፡፡ አበው በሃይማኖታቸው የሚበረቱ ደስ የሚሰኙባቸው፣ በሃይማኖታቸውም የደከሙ አርዓያ የሚያደርጓቸው ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ክርስቲያኖች እያሉ አብያተ ክርስቲያናት አይፈርሱም፣ አይደክሙም ይላሉ ይሏቸዋል፡፡ ባሕታዊው አባ መፍቅሬ ሰብእ “አጸድ የሌለው ደብር እና ጥምጣም የሌለው መምህር አንድ ናቸው” በሚለው ብሂላቸው አጸድ የሌላቸውን አብያተ ክርስቲያናት በአጸድ አስውበዋል፤ የገጠጡ ምድረ በዳዎችን በአረነጓዴ ካባ አጎናጽፈዋል፡፡
ባሕታዊ አባ መፍቀሬ ሰብእ ለዓመታት ገዳማትን እና አድባራትን አሳንጸው፣ በአጸድ አስውበው፣ በቅጽር አሳምረው ማረፊያ ሥፍራቸውን በደሴ አድርገዋል፡፡ እርሳቸው የደሴ ዋርካ ናቸው፣ እርሳቸው የደሴ አድባር ናቸው፡፡ በደሴ ሁሉም አባቴ ይላቸዋል፤ እሳቸውም ሁሉን ልጄ ይላሉ፡፡ በሃይማኖቱ አይመርጡም፤ ዘሩንም አይጠይቁም፤ እሳቸውንም በሃይማኖቴ አይመስሉኝም ብሎ የሚርቃቸው የለም፡፡
እኔም ያገኋቸው ደሴ ነው፡፡ አባ ትሕትናቸው አስገረመኝ፣ ደግነታቸው አስደነቀኝ፡፡ ከዬት ከዬት ተማሩ ባልኳቸው ጊዜ መልሳቸው “ኧረ እኔ አልተማርኩም” የሚል ነበር፡፡ ራሳቸውን የሚኮፍሱ በበዙባት ምድር እርሳቸው ግን ራሳቸውን ዝቅ ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ስንት አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሳነጹ፣ የስንት አብያተ ክርስቲያናትን ቅጽር እንዳስቀጸሩ፣ በስንት አብያተ ክርስቲያናት አጸድ እንደተከሉ በውል አይታወቅም፤ እሳቸውም በቸርነቱ ብዙ ነው ብለው ያልፋሉ እንጂ ቁጥሩን አይናገሩም፤ ዘመናቸውን በሙሉ ከእግዚአብሔር ደጅ አልራቁም፣ ጉልበታቸውን በዋዛ በፈዛዛ አላሳለፉም፤ በማዕልት ደብር ሲያስደብሩ፣ ቅጽር ሲያስቀጽሩ፣ አጸድ ሲተክሉ ይውላሉ፣ በሌሊት በጸሎት ተጠምደው በተጋድሎ ያነጋሉ፡፡
የበዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጹት፣ ቅጽራቸውን ያስቀጸሩት፣ በአጸድ ያስዋቡት ደገኛው አባት የሚወዷቸው ሁሉ ለእርሳቸው ማረፊያ ይሆን ዘንድ ቤት እንስራልዎት ባሏቸው ጊዜ “ቤቴ በሰማይ እንጂ በምድር አይደለም” በምድር የማርፍበት የእኔ የምለው ቤት አያሻኝም ነበር መልሳቸው፡፡
“እንኳን ሞት እርጅና አለ” እንዲሉ አሁን አርጅተዋል፣ እረፍትን የማያውቁት ባሕታዊ ደክመዋል፤ ሰውነታቸው ዝሏል፤ ከወትሮውም ለመናገር ቁጥብ ነበሩ፤ አሁን ደግሞ እርጅና አድክሟቸዋል፤ እርጅና ሳይጫጫናቸው፣ መናገር ሳይደክማቸው፣ የቀደመው ታሪክ ሳይዘነጋቸው ባገኛቸው ብዬ ተመኘሁ፡፡ ዳሩ አልሆነም፡፡ “ልረፍ አልልም፣ አይደክመኝም ነበር፣ አሁን ግን ደከምኩ” ብለውኛል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ማሰራት፣ እትክልት መትከል አልጠግብም ይላሉ።
እርሳቸው ምድርን ማስጌጥ፣ የተራቆተችውን ማስዋብ ይወዳሉ፣ ለዓመታትም ሲያስጌጧት ኖረዋል፡፡ ደኖችን አትመንጥሩ፣ ቅጠል አትበጥሱ እያሉ ዘወትር ያስተምራሉ፡፡ ደኖች የቅዱሳን አበው እና እመው መኖሪያ ናቸው፤ ቅዱሳን የእለት ምግባቸውንም ከደን ፍሬ ውስጥ ያገኛሉ፤ ያቺን በቀን አንድ ጊዜ እየቀመሱ፣ አምላክ ለሀገር ሰላም እና ፍቅር ይሰጠ ዘንድ ይማጸናሉ፤ ጤዛ እየላሱ፤ ድንጋይ እየተንተራሱ፤ የአራዊትን ድምጽ እየታገሱ ስብሐተ እግዚአብሔር እያደረሱ የሚኖሩ በደኖች ውስጥ ነው፤ ደኖች ሲመነጠሩ፣ ምድር እርቃኗን ስትቀር ቅዱሳን አበው ይርቃሉ፤ እነርሱ በራቁ ጊዜም ምድር የሚጸልይላት፣ ከማዕት እና ከመቅሰፍት የሚጠብቃት የለም ይላሉ አባ፡፡
ደን ለቅዱሳን፣ ለመናንያን፣ ለባሕታውያን እና ለሥውራን አበው ልብሳቸውም ጭምር ነው። በደኑ ተጠልለው፣ ከዓለም ርቀው ይኖራሉና፡፡ ደን የሀገር ግርማ ሞገስ፣ በረከትም ነው ይላሉ ባሕታዊ አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡ ለዚያም ነው ከልጅነት እስከ እርጅና ዘመናቸው ደረስ ዛፍ ከመትከል የማይቦዝኑት፡፡
አባ መፍቅሬ ሰብእ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለፍጠረታት ሁሉ ያዝናሉ፤ ይቆረቆራሉ፣ ፍጥረታትም ይወዷቸዋል፣ በእጃቸው አፈር ምሰው፣ ተክለው እና ተንከባክበው ባሳደጓቸው የዛፍ ጥላ ይጠለሉባቸዋል፡፡የሥነ ፍጥረታት ባለቤት እግዚአብሔር ያበቀለውን ደን አትመንጥሩ፣ ምድር ራቁቷን አታስቀሩ እያሉ በሰርክ ያውጃሉ፡፡ የአንዲት ቅጠል ያለ አግባብ መቆረጥ አብዝቶ ያሳዝናቸዋል፤ ያስለቅሳቸዋልም፡፡ ሰዎች ሁሉ ደን እንዳይቆርጡ ያስምላሉ፣ ቃል ኪዳን ያስገባሉ፣ እሳቸው ቃል ያስገቡት ሁሉ ዛፍ አይቆርጥም፣ ቃል ኪዳኑን አያፈርስም፣ ስለ ምን ቢሉ በምሐላ አስረውታልና፡፡
ጎዳናዎችን አጽዱ፣ ያማሩም አድርጉ፣ በጎዳናዎች ንጉሥ በሠረገላው ይጓዝበታል፤ ደኃም በባዶ እግሩ ያልፍ ያገድምበታል፤ ታቦታትም በክብር ያልፉበታል፣ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ኤጵስ ቆጶሳቱ፣ ካህናቱና ዲያቆናቱ፣ በጠቅላላው ሕዝብ ሁሉ ይመላለስበታልና ነው የሚሉት አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡
በአንድ ወቅት የደሴ ደብረ ቤቴል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እየተሠራ የማሰሪያ ገንዘብ አጠረ አሉ፡፡ አሰሪ ኮሚቴው መላ አጣ፡፡ ተጨነቀ፡፡ ከብዙ ጭንቀት በኋላም ሰው የሚወዳቸውን አባት መሸጥ ፈለጉ፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብእንም አማከሯቸው፡፡ “አባ የእርስዎን ፎቶ ሸጠን የቤተክርስቲያን ማሰሪያ ገንዝብ ልንሰበስብብዎት ነው፣ ምን ይላሉ?” አሏቸው፡፡ እሳቸውም በሚታወቁበት ትሕትናቸው “ እኔን ማን ይገዛኛል፣ ምንስ አወጣለሁ” አሉ፡፡ እነርሱም እርሳቸው ፈቃደኛ ከሆኑ ሌላው ችግር እንደሌለው ነገሯቸው፡፡ አባም “ለቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ ካወጣሁስ እንኳን ፎቴዬን እኔንም ሽጡኝ አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግማችሁ ሽጡኝ” አሉ፤ ፎቷቸውም ለጨረታ ቀረበ፡፡ መወደድን በጠዋቱ ተችረዋልና፣ ተወደዱ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይም ፎቷቸው ተሸጠ፡፡ ደብሩም አምሮና ተውቦ ተሠራ፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ብዙዎች “የተሸጡት አባት” ይሏቸዋል፡፡ “ብዙዎች በጎችን ይሸጣሉ፣ እሳቸውን ግን ለበጎች ይሸጣሉ” ሲሉም ይገልጿቸዋል፡፡ ስለሞት ሲያስቡ ምን ያስጨንቀወታል በተባሉ ጊዜ ከአብያተ ክርስቲያናት መለየቴ ያስጨንቀኛል ይላሉም አሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!