
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደጋጎች ለሀገር ሰላም ይማጸኑበታል ፤ ለሕዝብ ፍቅር ዱዓ ያደርጉበታል። ፈጣሪ ለምድር በረከቱን እና እዝነትን ይሰጥ ዘንድ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁበታል ፤ ያለ ማቋረጥ ሶላት ይሰግዱበታል ፤ ቁራዓን ይቀሩበታል። ፈጣሪያቸው አላህን ያስታውሱበታል ፤ የተወደደውን ነገር ሁሉ ያደርጉበታል ፣ መሻይኮች ይገናኙበታል ፣ ኢማሞች በክብር ያሰግዱበታል ፤ ደረሳዎች ከሊቆቹ እግር ሥር ተቀምጠው ሃይማኖትን ይማሩበታል፡፡
በዚያ ባማረ እና በተዋበ የአላህ ቤት የአላህ አገልጋዮች አይታጡበትም፣ ዱዓ አይቋረጥበትም፡፡ ዕውቀት አይነጥፍበትም፣ መሻይኮች፣ ኢማሞች፣ ኡስታዞች ዕውቀትን ያፈስሳሉ። ደረሳዎች ከሚፈስሰው ዕውቀት ያለ ማቋረጥ ይጎነጫሉ ፤ እየተጎነጩም ከጥማቸው ይረካሉ ፣ የፈጣሪን ጥበብ ያስታውሱበታል፡፡
ያቺ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት፣ የሰላም እመቤት ውቧ ከተማ በተነሳች ቁጥር ስሙ አብሮ ይነሳል ፤ እርሷ በታወሰች ቁጥር አብሮ ይታወሳል፡፡ በዚያች ውብ ከተማ ከእርሱ ቀድሞ የተሠራ መስጊድ የለም ይባላል፡፡ ለከተማዋ ፍቅር የሚያስተምሩ ፣ ለሀገር ፍቅር ቃል ኪዳን የሚያስሩ ፣ አንድነትን የሚያጸኑ ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ፣ አብሮነትን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ አባቶች ሲፈልቁበት ኖረዋል ፤ እየፈለቁበትም ነው፡፡
አሠራሩ ድንቅ ነው ፤ የጥንቱ ውበቱ አልደበዘዘም። ዛሬም ከነውበቱ ፣ ዛሬም ከነግርማ ሞገሡ በግርማ ይታያል። በአሻጋሪ ለተመለከተው ፣ ቀርቦም ላየው ደስታን ይሰጣል ፤ የትናንትን ጥብበ ከዘመናት በኋላ ያሳያል። የቀድሞ አባቶችን ድንቅ ዕውቀት ይመሰክራል ደሴ ሸዋበር መስጊድ፡፡
ሸዋበር መስጊድ ረጅም ታሪክ የሚመዘዝለት ፣ የዓመታት እድሜው የሚነገርለት ፣ ድንቅ ጥበብ ያለበት ታላቅ መስጊድ ነው፡፡ በመስተምሥራቅ የንጉሥ ሚካኤል ቤተመንግሥት ፣ በስተምዕራብ የጦሳ ተራራ ያጅቡታል ፤ በአሻገሪ ኾነው ይመለከቱታል፡፡
ከመካከላቸው ድንቅ ኾኖ የተሠራው ፣ ከፍ ብሎ የሚታየው ሸዋበር ለደሴ ውበትን ፣ ሃይማኖትን ፣ አንድነትን ፣ ኢትዮጵያዊነትን ፣ ፍቅርን ፣ ሰላምን ፣ ደስታን ያስተምራል፡፡ ወደ ከተማዋ ለመጡ ሁሉ ታሪክን ይነግራል ፤ ትናንትን ከዛሬ እና ከነገ ጋር እያጋመደ ሕያው ኾኖ ይመሰክራል ፤ ሕያው ኾኖ ያስተሳስራል፡፡
ያቺ በታሪክ የጠገበች ፣ በፍቅር የተሞሸረች ፣ በአብሮነት የተዋበች ፣ የሰላም ምሳሌ የኾነች ውብ ከተማ ታሪክ ተዝቆ አያልቅባትም፡፡ ስለ አንደኛው ሲናገሩ ሌላ ትደርባለች ፤ ድንቅ ታሪክ ታመጣለች ፤ ከታሪክ ላይ ታሪክ ትጨምራለች፡፡
በደሴ ጎዳናዎች የተመላለሰ ሁሉ ፍቅርን ይገበያል ፤ ሰላምን ያገኛል፡፡ በደሴ ሰማይ ሥር ኢትዮጵያ ትደምቃለች፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ከፍ ትላለች፡፡ እንኳን ሰዎቹ ይቅርና ጭሱ ሳይቀር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ይላል። በኢትዮጵያ ሠንደቅ ተውቦ ውሎ ያድራል ፤ በአሻገር ሲያዩት ገና ልብን በደስታ ይገዛል ፤ በፍቅር ያስራል፡፡
ሁሉንም በደስታ እና በፍቅር እየተመለከትኩ ፣ ከደጋጎቹ ጋር በጎዳናዎች እየተጓዝኩ ወደ ታሪካዊ መስጊድ አቀናሁ፡፡ ሸዋበር በደሴ ከተማ የመጀመሪያው መስጊድ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡ ታሪኩን እያንሰላሰልኩ ፣ ከፍ ብሎ የሚታየውን የሸዋበር ሚናራ በአሻገር እየተመለከትኩ ገሰገስኩ፡፡ ሸዋበር ገና በአሻገር ሲያዩት በውበቱ ይጣራል፡፡ በውበቱ እየተሳብኩ በግርጌው ደረስኩ፡፡
በሸዋበር መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ኾነው ሚናራውን ወደ ላይ ሲመለከቱት ከጦሳ ተራራ ጋር ተለካክቶ የቆመ ይመስላል፡፡ ጦሳን ፈጣሪ ውብ አድርጎ ሠርቶታል ፤ ሸዋበርን ደግሞ ፍጡራን ፣ የአላህ አገልጋዮች ውብ አድርገው አሳምረውታል፡፡ ሁለቱም ለዚያች ከተማዋ ውበቶች እና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከታላቁ መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆሜ ታሪኩን ጠየኩ ፤ ታሪክ አዋቂዎችም ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ነገሩኝ፡፡
የሸዋበር መስጊድ ወጣቶች ሰብሳቢ እና የመስጊዱ ታሪክ አዋቂ ከድር አሊ ታሪኩ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ይመዘዛል ብሎኛል፡፡ በከተማዋ ይኖሩ የነበሩ ሙስሊሞች በእድር አማካኝነት የአላህን ቤት ለመገንባት ጀመሩ፡፡ እነርሱ ለመሥራት በሚታትሩበት ወቅት ደገኛ አባት አገኙ፡፡ አሁን ያለውን የተዋበ ኪነ ሕንጻ ያለበት መስጊድ በዚያ ዘመን አጠራር ከኤርትራ ክፍለ ሀገር በአሁኑ አጠራር ከሀገረ ኤርትራ የመጡ ሼህ ሰይድ ኪኪያ የሚባሉ አባት ደጋግ አማኞች ያስጀመሩትን መስጂድ አጠናቀቁት ይባላል፡፡ የሸዋበር መስጊድ የጥንት አሠራር በተነሳ ቁጥርም የሼህ ሰይድ ኪኪያ ስም አብሮ ይነሳል፡፡
በዚያ ዘመን ታሪካዊውን መስጊድ ሠርቶ ለማጠናቀቅ 53 ማር ትሬዛ እንደጨረሰም ይነገራል፡፡ አሠራሩ ድንቅ ጥበብ ያረፈበት ፣ የታላላቅ አባቶች ዕውቀት የተገለጠበት ነው፡፡ ታሪክ አዋቂ ሲነግሩኝ እጅግ የሚደንቅ ጥበብ ያለበት መስጊድ ነው ይላሉ፡፡ አሠራሩ የመስጊዱን ግድግዳ ዝናብ እንዳይመታው ተደርጎ የተሠራ ፣ ዛሬ ላይ ያለውን ጥበብ እና የሕንጻ አሠራር ጥበብ የሚያስነቅ ነው ይሉታል፡፡
ዝናቡ መሬት ላይ አርፎ እየተፈናጠረ የመስጊዱን ዋና ክፍል እንዳይመታው በተዋበ ጥበብ የተሠራ ድንቅ ጥበብም አለበት፡፡
እጅግ ባመሩ ጥርብ ድንጋዮች ፣ እጅግ በሚያምሩ የእጅ አሻራዎች አሳምረው ሠሩት፡፡ ለድንጋይ ድንቅ ውበት ሰጡበት ፤ ድንጋይ በድንጋይ አቀጣጥለው የአላህን ቤት አሳመሩት ፤ የአላህን ቤት አስዋቡት፡፡ በዚያ ዘመን አምሮና ተውቦ እንደተሠራ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አይነት እድሳት አልተደረገበትም ነው ያሉኝ፡፡
ውበቱ ሳይደበዝዝ እንደ አማረ እና እንደ ተዋበ አሁን ድረስ አለ፡፡ አምረው የተሠሩት ድንጋዮች አልተቦረቦሩም፣ አልተዛነፉም እንደ ቀደመው ሁሉ ከነውበታቸው ተቀምጠዋል እንጂ፡፡ ሸዋበር ያረፈበት ቦታ አስቀድሞ ገና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ ታሪክ የሠሩበት እና ለሃይማኖታቸው በብርታት የታዩበት ፣ መሥዋዕትም የከፈሉበት እንደኾነ ታሪክ አዋቂው ነግረውኛል፡፡
ሸዋበር መስጊድ ከደሴ ወደሸዋ አቅጣጫ በሚያስወጣው በር በኩል የተሠራ ነውና ከዚያ አንጻር ስሙ የመጣ እንደኾነም ይነገርለታል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚገባበት፣ አስመራ ድረስ የሚሄድበት ዋናው መሥመርም በሸዋበር መስጊድ አጠገብ ነው ብለውኛል፡፡ ታላቁ መስጊድ የበዙ ታሪኮችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡
በዚያ ታላቅ መስጊድ ውስጥ የቁርዓን ተፍሲር ፣ የአረብኛ ትምህርት ፣ የሀዲስ ትምህርቶች ይሰጡበታል፡፡ ጀንበር ዘልቃ በጠለቀች ቁጥር መምህራን እና ተማሪዎች ይገናኙበታል ፤ ሃይማኖትን ይማሩበታል፡፡ በአንድነትም ዱዓ ያደርጉበታል፡፡ በዚያ መስጊድ ውስጥ ቤት ይቁጠራቸው የሚባሉ፣ ሊቅነታቸው አንቱ የተባለ ፣ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ መሻይኮች እንደወጡበትም ታሪክ ነጋሪው ነግረውኛል፡፡
ሃይማኖትን ለመማር ልቡ የፈቀደ ሁሉ ወደ መስጊዱ ይጓዛል ፤ መሻይኮችም በፍቅር ተቀብለው ፣ በሚጣፍጥ አንደበታቸው ያስተምራሉ፡፡ ዕውቀትን ያለ ማቋረጥ የሚያጠጡት አባቶች ክፍያቸውን ከአላህ እንጂ ከሰዎቸ አይጠብቁም፡፡ አላህን እያሰቡ ያስተምራሉ ፤ ባስተማሩም ጊዜ ደስ ይሰኛሉ፡፡ ይህ ሥርዓት አሁን ድረስ በዚያ መስጊድ ውስጥ አለ፡፡
ሸዋበር መስጊድ ባለው ታሪክ ልክ ያልተነገረለት ፣ ያልተመሰከረለት ፣ ጎብኚዎች ያልሄዱበት ነው፡፡ ሃይማኖቱን የሚከተሉ ብቻ ሳይኾን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያዩት ፣ ታሪኩን ሊሰሙለት እና ሊነግሩለት የሚገባም መስጊድ ነው፡፡
ሰው ሃይማኖት ሲኖረው ስጋዊ ፍላጎቱን ይገታል ፤ ወደ ነብሱ ያዘነብላል። ነብሱን ባሰበ ፣ ፈጣሪውን ባስታወሰ ቁጥር ደግሞ ፍቅርን ፣ ሰላምን ፣ አንድነትን ያውጃል። በሰዎች መካከል ግንኘነትን ያጠናክራል ፤ ሃይማኖት እንዲኖረው ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ሊጠበቁ ይገባቸዋል ነው ያሉኝ ታሪክ ነጋሪው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ሲኖሩ ዕውቀት ይኖራል ፤ ታሪክ ይነገራል ፤ ፍቅር እና ሰላም ይሰበካል፡፡ የሃይማኖት ትምህርቶች እንዳይቋረጡ መሠራት አለበትም ብለውኛል፡፡ ሸዋበር መስጊድ ሁልጊዜም ሶላት የሚሰግዱ አማኞች አይጠፉበትም፡፡ በተለይ ግን የጁመዓ ቀን ሸዋበር መስጊድ በሰዎች ይሞላል ፤ ስለ ሀገር ፍቅር ፣ ስለ ሀገር ሰላም በሚበረቱ ፣ ሶላት በሚሰግዱ አማኞች ይጨነቃል፡፡ ከመስጊዱ ቅጥር ግቢ አልፎ በዙሪያው ባሉ ሥፍራዎች ሁሉ የሃይማኖቱ ተከታዮች ተሰብስበው በጀመዓ ሶላት ይሰግዳሉ፡፡
በሸዋበር መስጊድ ውስጥ ትውልድ ሁሉ የሚማርበት ፣ ሃይማኖቱን ፣ ታሪኩን እና ሌሎች ዕውቀቶችን የሚያውቅበት ቤተ መጻሕፍትም አለበት፡፡ ሸዋበር መስጊድ ችግር በተፈጠረ ጊዜ እርቅ ይደረግበታል ፣ ሰዎች ባለፉ ጊዜም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጸምበታል ነው ያሉኝ፡፡
ደሴ ውስጥ የሃይማኖት ልዩነት አይነሳም ፤ በአንድ ቤት ውስጥ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ይኖራሉ። ሃይማኖታቸውን በሚያምኑበት ያመልካሉ ፤ ኑሯቸውን ግን በጋራ ይኖራሉ። ይህ እንዲኾን ያደረጉት ደግሞ ብልህ አባቶች፣ እናቶች የሠሩት የቆዬው ሥርዓት ነው፡፡
ታሪክ አዋቂው ሲነግሩኝ ወሎ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ተጋብተው ይኖሩባታል ፤ ሚስት ወደ ቤተክርስቲያን ስትሄድ ልጆቿን ይዛ ትሄዳለች ፣ ልጆቿ ቤተክርስቲያን ተምረው ይመለሳሉ፣ አባት ወደ መስጊድ ሲሄድ ልጆቹን ይዞ ይሄዳል ፣ መስጊድ ተምረው ይመጣሉ። ልጆች የአባት እና እናታቸውን ሃይማኖቶች በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ባወቁም ጊዜ በምርጫቸው የኔ ብለው የፈለጉትን ሃይማኖት ያመልካሉ፡፡ ይህ የነበረ እና ያለ እሴት ነው ብለውኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የታላላቅ አባቶች መኖር ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡
አጥኚዎች የወሎን ድንቅ እሴት ማጥናትና ማስተማር አለባቸው፣ የቆዬው እሴት አሁን ባለው ነባራዊ ሃቅ እንዳይወድቅም ጥንቃቄ መደረግ አለበት ነው ያሉኝ፡፡
በሸዋበር መስጊድ ውስጥ ኾኜ ድንቅ ታሪክ ሰማሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም ፣ አንድነት ፣ ፍቅር እና ደስታ የሚተጉ አባቶችን አየሁ፡፡ ባየሁት እና በሰማሁትም ተነደቅሁ፡፡ ሂዱና ተመልከቱት ሃይማኖትን ፣ ታሪክን ፣ እሴትን ትማሩበታላችሁ ፤ ደስታን ታገኙበታላችሁ፡፡ ሸዋበር የደጋጎች መማጸኛ ፣ የመሻይኮች መገናኛ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!