“የጉበት በሽታ ምንድን? መከላከያ መንገዱስ”

71

ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጉበት በሽታ ኹሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ነው። በሽታው ከሰዎች ወደ ሰዎችም በቀላሉ ይተላለፋል።

ከሰውነት ክፍላችን ውስጥ ከቆዳ ቀጥሎ ትልቁ ክብድት ያለው ለጉበት ነው። ጉበት 1 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ይመዝናል። በሰው ልጅ የሆድ እቃ ውስጥ ትልቅ ሥራ ካላቸው የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ጉበት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል።

በርካታ ተግባራት ያሉት ጉበት ምግብም ኾነ መድኃኒት ብንወስድ ቀድሞ የሚደርሰው ጉበት ላይ ነው። ጉበትም አጣርቶ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያሠራጫል።

ይህ ኹሉ ተግባር የተጣለበት እና በርካታ ተግባር ያለው ጉበት በጀርሞች፣ በቫይረሶች፣ በትላትሎች፣ በቫክቴሪያዎች እና በፈንገሶች እንዲኹም በመድኃኒቶች፣ በአደንዛዥ እጾች (በሲጋራ፣ ጫት)እና በአልኮል ጉዳት ይደርስበታል።

እነዚህ ወደ ጉበታችን ከደረሱ እንደየመጠናቸው ጉዳት ያስከትላሉ።

የድሪም ኬር ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መኮንን አይችሉህም ለጉበት በሽታ ስለሚያጋልጡ ነገሮች፣ የጉበት በሽታን ስለሚያባብሱ እና የጉበት በሽታን እንዴት መከላከል እንደሚቻል በዝርዝር አስረድተዋል።

በተለይ ሄፕታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ እና ዲ የተባሉ ቫይረሶች ጉበትን በመጉዳት ከከፍተኛ ሕመም እስከ ሞት የሚያደርሱ ናቸው ብለዋል።

“ሄፕታይተስ ኤ” የተባለው ቫይረስ ሕጻናትን የሚያጠቃ የቫክቴሪያ ዓይነት ነው። በበቂ መጠን ንጹህ ውኃ በሌለበት እና ንጽሕናው ባልተጠበቀ አካባቢ የሚኖሩ ሕጻናት ለችግሩ ተጋላጭ ይኾናሉ።

ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉት ደግሞ አዋቂዎችን የሚያጠቁ የቫይረስ አይነቶች ሲኾኑ የሻገተ እንጀራ በተደጋጋሚ በመብላት፣ አልኮል መጠቀም፣ ለሱስ በመጋለጥ፣ ሲጋራ በማጨስ፣ ያልታዘዙ መድኃኒቶችን በተከታታይ በመውሰድ የሚመጡ ናቸው ይላሉ።

ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉት የጉበት በሽታዎች ተላላፊ ሲኾኑ የመተላለፊያ መንገዳቸው ደግሞ ልቅ የኾነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታማ ነገሮችን በጋራ በመጠቀም፣ ባልተገባ የደም ንክኪ ይተላለፋሉ።

ኤች አይ ቪ በሚተላለፍባቸው መንገዶች ኹሉ የጉበት በሽታ ከሰዎች ወደ ሰዎች ይተላለፋል እንደሚተላለፍ ዶክተር መኮንን አስረድተዋል።

የአኗኗር ዘይቤያችን ያልተስተካከለ ከኾነ ጉበት ሊመጣ ይችላል የሚሉት ዶክተሩ በቂ የኾነ ንጹህ የመጠጥ ውኃ፣ መጸዳጃ ቤት በአግባቡ አለማግኘት ለበሽታው መከሰትም መተላለፍም ዋነኛ መንገድ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ሕጻናትን የሚያጠቃው ሂፐታይተስ ኤ የተባለው የጉበት በሽታ ወደ ብዙ ሕጻናት ሊሸጋገር ይችላል።

የጉበት በሽታን መከላከል እንደሚቻል የተናገሩት ዶክተር መኮንን ማንም ሰው ከመጸዳጃ ቤት ውጭ ባለመጸዳዳት፣ ንጽሕናው በተጠበቀ አካባቢ በመኖር፣ በአካባቢው በቂ ንጹሕ የመጠጥ እንዲኖር በማድረግ፣ በሀኪም ያልታዘዙ መድኃኒቶችን ባለመውሰድ፣ ከአልኮል መጠጥ እና ከሱስ ነጻ በመኾን መከላከል ይቻላል ብለዋል።

እንዲኹም ለበሽታው ተጋላጭ የኾነን ሰው በሽታውን ለሌሎች እንዳያስተላልፍ፣ የራሱ ሕመም የከፋ ጉዳት እንዳያደርስበት በጥንቃቄ የሚኖር ከኾነ በሽታውን መከላከል ይቻላል ብለዋል።

ሌላው እና ዋናው የመከላከያ ዘዴ ክትባት ነው ያሉት ዶክተር መኮንን በሽታው የጀመረው ሰው ክትባት ቢወስድ መዳን እንደማይችል አስጠንቅቀዋል።

አንድ ሰው ክትባቱን ለመውሰድ ተመርምሮ ከጉበት በሽታ ነጻ መኾኑን ማረጋገጥ እንዳለበት እና ክትባቱን ለሦስት ተደጋጋሚ ጊዜ መውሰድ እንደለበት አሳስበዋል።

የጉበት በሽታ አምራች የኾነውን የሰው ልጅ ሕይወት እየነጠቀ ያለ በመኾኑ ማንኛውም ሰው የአኗኗር ዘይቤውን በማሻሻል፣ አመጋገቡን በማስተካክል ከአልኮል እና ሱስ ከሚያመጡ ነገሮች ራሱን በመጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎበኙ።
Next article“ሸዋበር የደጋጎች መማጸኛ፤ የመሻይኮች መገናኛ”