
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፋሊያ የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል፡፡ የኢፌዴሪ አየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ከዓለም በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ የላቀ ስም ካላቸው ሀገራት አንዷ ከሆነችው የቼክ ሪፐብሊክ ጋር ተቋማዊ ትስስሮችን ለማጠናከር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
አጋጣሚው አየር ኃይሉ በሪፎርሙ የአቪዬሽን ትጥቆችን ለማዘመን እያከናወነ ላለው ዘርፈ ብዙ ተግባራትና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማሳደግ እደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከቼክ መንግሥት ጋር በተለያዩ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ ተባብሮ የመስራት የረጅም ጊዜ ልምድና መልካም ግንኙነት እንዳለው አንስተዋል፡፡
ሀገራቱ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተጀመሩትን የሰው ኃይል አቅም ሥልጠና እና ሌሎች የሙያ መስኮችን ለማስቀጠል መስማማታቸውም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፋሊያ ከቼክ ሪፐብሊክ የመጡ የአቪዬሽን ሙያተኞች ከኢትዮጵያውያን ጋር በአቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ያከናወኑትን የአውሮፕላኖችን ዕድሜ የማራዘምና እድሳት ሥራ አድንቀዋል፡፡
በተጨማሪም በበረራ ትምህርት ቤት ሲሙሌተር (ምስለ በረራ) ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎችንም ተመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ጉዞ መደነቃቸውንም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አስፍሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!