
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር በስሩ ካሉ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ተሳታፊዎች “መፈታት ይገባቸዋል” ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል። ሰላም የሁሉም መሠረት መኾኑን ያነሱት ተሳታፊዎች የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ለረጅም ዓመታት ምላሽ ባለማግኘታቸው አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት መኾኑን አንስተዋል። የሕዝብን ጥያቄዎች እስከ ታች ወርዶ በመለየት ፈጥኖ መፍትሔ መስጠት ይገባል ብለዋል።
የዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዲከበር እና ፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት እንዲኖር ጠይቀዋል።
በየተቋማቱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መኖሩን ያነሱት ተሳታፊዎች ችግር ያለባቸውን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎችን በመለየት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባልም ብለዋል። ነገ ላይ እልባት ለሚሰጠው ጉዳይ ዛሬ ላይ የሰው ሕይዎት መጥፋት እና የንብረት ውድመት መድረስ እንደሌለበት ነው የተናገሩት።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሀሰተኛ ትርክት የአማራ ሕዝብ ተገድሏል ፤ተፈናቅሏል ብለዋል። በአማራ ሕዝብ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲፈቱ የክልሉ መንግሥት እንደ መመሪያ እና ደንብ አድርጎ እየሠራ መኾኑንም አቶ ሲሳይ አንስተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከሌሎች ክልሎች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት። በሕዝቦች ላይ ለሚደርሱ ችግሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
“የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። የመንግሥት ሠራተኛውም ለሕዝቡ የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት መደማመጥ እና መከባበር ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ክልሉ አሁን ካለበት የሰላም እጦት በመውጣት ወደ ልማት እና ወደ ተረጋጋ ሰላም እንዲመለስ በጋራ መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!