የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

50

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ገልጿል። ለእንስሳት ሃብት ልማት ምቹ ከኾኑ አካባቢዎች መካከል ሰሜ ሸዋ ዞን አንዱ ነው፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ እስከ ጣርማ በር ያለው አካባቢ በጥምር ግብርና ምቹነቱ የሚገለጽ ሲኾን ከፍተኛ የወተትና የሥጋ ተዋጽኦ ማግኘት የሚያስችል እምቅ አቅም አለው።

በሰሜን ሸዋ ዞን በዓመት ከ80 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት እንደሚመረት ይነገራል። ከደብረ ብርሃን እስከ አዲስ አበባ ያለውን የአስፓልት መንገድ ብቻ ተከትሎ በቀን ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ሊትር ወተት እንደሚገኝም ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ እየተገኘ ያለው የወተት ምርት ካለው የምርት አቅም አንጻር በጣም አናሳ እንደኾነ በተደጋጋሚ ይገለጻል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የወተት ምርታማነትን ለመጨመር በ4 ወረዳዎች ላይ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

የእንስሳት ዘርፉን የተሻለ ምርታማ ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ዝርያ ማሻሻል፣ የተሻሻለ መኖ ማቅረብና የተጠቃሚ ማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም ኮሪያን ፍሪጂያን ሴመን የተሰኘ ዘረመልን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ አሥታውቋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምር ማኅበረሰብ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የእንሰሳት ልማት፣ ምርምርና ሥርፀት ዳይሬክተር ዮሐንስ ሙሉነህ (ዶ.ር) እንዳሉት 30 ሺህ ዶዝ ዘረመል ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል። ከዚህ ውስጥ ዩኒቨርሲቲው 1 ሺህ 5 መቶ ዶዝ በመውሠድ በአራት ወረዳዎች እየሠራ እንሚገኝ አመላክተዋል።

ከዩኒቨርሲቲው በተገኘ መረጃ መሰረት የመንዝ በግ ዝርያ ማሻሻል ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው። እስካኹን በደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ለ20 ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል።

የበጎችን የስጋ ምርታማነት ደረጃ በአርሶ አደሮች አሠራር ከ17 ኪሎ ግራም ወደ 23 ኪሎ ግራም ያሳደገ ሲኾን በምርምር ማእከሉ ደግሞ ወደ 26 ኪሎ ግራም ማሣደግ ተችሏል። ዩኒቨርሲቲው ተደራሽ ባልኾኑ ወረዳዎች ላይ በትኩረት እየሠራ እንደኾነ ተጠቅሷል።

ሥራዎችን ውጤታማ በማድረግ ሂደቱ የአርሶ አደሮችን ግንዘቤ ማሣደግም ሌላኛው ተግባር እንደኾነ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተማሪዎችን አንቀበልም አላልንም” በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም
Next article“የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው” ሲሳይ ዳምጤ