
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል የሚገኙ ዪኒቨርሲቲዎች ፎረም ተማሪዎችን አንቀበልም ብለዋል በሚል መረጃዎች ሲሰራጩ ሰንብተዋል፡፡
ዪኒቨርሲቲዎች ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሠረት ተማሪዎችን አንቀበለም፣ ይህ ደግሞ አቋማችን ነው አሉ የሚል መረጃ ነው የተሰራጨው ፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረምን አነጋግሯል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ አስማረ ደጀን (ዶ.ር) የአማራ ክልል ዪኒቨርሲቲዎችን አቋም በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው መረጃ የተሳሳተ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ጸሐፊው የተሰራጨው መረጃ በአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ያልተባለ ነውም ብለዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዪኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል አመች ኹኔታዎችን እየተጠባበቁ መኾኑን ዶክተር አስማረ አንስተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ዪኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን መጥራት መጀመራቸውን ገልጸው፤ ወሎ ዪኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ጥሪ ማስተላለፉን ለአብነት አንስተዋል፡፡
አብዛኞቹ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እየጠሩ ነው፤ ብዙ ተማሪዎችን በአንድ ጊዜ ለመጥራት ግን የግብዓት ችግር ለተቋማቱ እንቅፋት ኾኗል ብለዋል።
በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ግብዓት አቅራቢዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለማቅረብ መቸገራቸውን አንስተዋል፡፡ ቢኾንም ዪኒቨርሲቲዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው በየአካባቢው ያሉ አቅራቢዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን ተቀበሉ በሚልበት ጊዜ የማይቀበሉበት ምክንያት የለም ብለዋል ዶክተር አስማረ፡፡
ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ ከመጣ ተቋማቱ ተማሪዎቻቸውን ወዲያው ይጠራሉ፤ ተማሪዎችን አይጠሩም የተባለው ስህተት ነው፤ አልተባለምም ሲሉ አስረግጠዋል፡፡
ሃሰተኛ መረጃ ያሰራጩ የብዙኀን መገናኛ ተቋማትም ማስተካከያ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አንዳንድ ዪኒቨርሲቲዎች ግብዓት ለማግኘት ከመቸገራቸው ውጭ የመማሪያ ክፍሎችን አጽድተዋል፣ እድሳት የሚያስፈልጋቸውንም አድሰው ለትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ዝግጁ ኾነዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!