
አዲስ አበባ: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን ማኅበረሰባዊ ትስስር መልሶ ለመገንባት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያለመ ምክክር በአዲስ አበባ እየተካሔደ ነው።
ምክክሩ “የድረህ ግጭት ለውጥ በኢትዮጵያ” የሚል መሪ ሃሳብ የያዘ ሲኾን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው። መቀሌ እና ሰመራ ዩኒቨርሰቲዎችም የምክክሩ ተባባሪዎች ናቸው ተብሏል።
የዚህ ምክክር ዋና ዓላማ በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች የሰላም ግንባታ እና ዘላቂ እርቅን ማምጣት ነው። በሦስቱ ክልሎች ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን እና ፈተናዎችን መለየት እና የጋራ ተግባራዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማፈላለግም የውይይቱ ዓላማዎች ናቸው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት ማኅበረሰባችን ፈትኗል፤ መሠረተ ልማቶቸን አውድሟል፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችንንም በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል ብለዋል። ወሎ፣ ወልደያ እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች ከአማራ ክልል የተጎዱ ሲሆን ከትግራይም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት።
ዶክተር መንገሻ የመልሶ ግንባታ ተግባሩን በጋራ እና በመተባበር መሥራት ይገባል ብለዋል። “የሕዝቦችን የቀደመ ማኅበረሰባዊ ትስስርን መልሶ በማጠናከር የወደሙ ተቋማትን በትብብር መገንባት ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ቱሽኔ ስለሰላም ግባታ እና ማኅበረሰባዊ ትስስር ተሰባስበን መምከር መጀመራችን መልካም ጅማሮ ነው ብለዋል። ግጭትን በባሕላዊ መንገድ በመፍታት ማኅበረሰባዊ ትብብር እና ልማትን በጋራ ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ፖለቲካዊ ይቅር ባይነትን በማሳደግ ለሰላም እና ለእርቅ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ.ር)፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፋና ሀጎስ (ዶ.ር) እና የዩኖቨርሲቲዎቹ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ዑስማን፤ የብሔራዊ ምክከር ኮሚሽን አባለት እና የሦስቱ ክልሎች የመንግሥት ተወካዮች እንዲሁም የማኅበረሰብ ተወካዮ በምክክሩ ላይ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!