
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኛው ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል። በተጨማሪም አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንደሚገባም ተጠይቋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ ከሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት መሰብሰብ የነበረበትን ግብር መሰብሰብ አልተቻለም፤ በከተማው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም ተቋርጠዋል።
የክልሉን ሰላም በማጽናት አሁን ላይ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት እና የተቋረጡ ፕሮጀክቶችም ወደ ሥራ እንዲገቡ የመንግሥት ሠራተኛው ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ የውይይት መነሻ ሀሳቦች ቀርቧል። የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሥራት፣ የልማት ሥራዎችን ማሻሻል፣ የገቢ አቅምን ማጠናከር፣ መልካም አሥተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ይገባል ተብሏል።
የቅንጅት እና ትብብር ሥራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኅብረተሰብን ተሳትፎ ማረጋገጥ ዋናው የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ተቀምጧል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!