”በ2016 በጀት ዓመት በአፍሪካ ደረጃ ቢያንስ አንድ ጨረታ አሸንፈን ለመሥራት አቅደናል” ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን

45

ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን በውኃ፣ መንገድ እና ህንጻ ሥራዎች ግንባታ የጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የግንባታ ክትትልና ውል አሥተዳደር ሥራ ላይ የተሰማራ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።

ኮርፖሬሽኑ በግሉ ዘርፍ ያለውን ውስንነት ሸፍኖ በመሥራት የልማት እና የገበያ ክፍተቶችን በመሙላት ሕዝብን ተጠቃሚ የማድረግ ተልዕኮ ያለው መኾኑን የኮርፖሬሽኑ የገበያ ልማት እና ኮምዩኒኬሽን ኀላፊ ታደሰ በላይ ጠቅሰዋል።

”እስካሁን ድረስ ከ3 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፈን በውጤት አጠናቀናል” ያሉት አቶ ታደሰ በሂደት ላይ ያሉ እና ኮርፖሬሽኑ የሚሳተፍባቸው 200 የልማት ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

አቶ ታደሰ ኮርፖሬሽኑ ከአማራ ክልል ውጪ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሶማሌ ክልሎች በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ነው የገለጹት። የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እምነት ጥለውብን በውጤት ፈጽመናል፤ በአሠሪዎች በኩልም ጥሩ እውቅና እና ግንኙነት አለን ብለዋል።

”ለተቋቋምንበት ዓላማ እና በገባነው ውል መሰረት በሥነ ምግባር እሴቶቻችን እየተመራን በጥራት እና በውጤታማነት እንሠራለን” ያሉት አቶ ታደሰ ለገበያ እና ለመልካም ስም ኮርፖሬሽናቸው ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያመላከቱት።

ኮርፖሬሽናቸው ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቆ በተወዳዳሪነት ለመሥራት መደራጀቱን የገለጹት የገበያ ልማትና ኮምዩኒኬሽን ኀላፊው በምስራቅ አፍሪካ ተወዳድረን አሸናፊ ለመኾን የዓለም አቀፍ ደረጃዎች (አይ ኤስ ኦ) አሟልተን በመሥራት ሂደት ላይ ነን ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም በአፍሪካ ቢያንስ አንድ ጨረታ አሸንፈን ለመሥራት አቅደናል ነው ያሉት።

ለጥራት ትኩረት በመስጠት፣ በጥናት እና ምርምር የታገዘ ሥራ ለመሥራት እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥራዎችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ማቀዱን አቶ ታደሰ ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል:-

👉 በጸጥታ መደፍረስ የሥራዎች መቆም፣

👉 የትላልቅ መሣሪያዎች እጥረት፣

👉 የአቅም ውስንነት፣

👉 ኮንትራክተሮች በውላቸው መሰረት ካልፈጸሙ በኮርፖሬሽኑ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተጠቃሾች መኾናቸውን አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የጸጥታ መደፍረስ ባለባቸው አካባቢዎች ተቋራጭ መግባት ባለመቻሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሥራ መቋረጣቸው እና በአዲስም መጀመር አለመቻሉን ነው ኀላፊው የተናገሩት።

ልህቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን አሁን ላይ ለ974 ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ሲኾን አንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል አለው።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይገባል” የምእራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የትንተና እና ትንበያ ባለሙያ አቶ መልካሙ በላይ
Next articleየመንግሥት ሠራተኛው ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ ቀረበ።