
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችን እየተከሠተ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊቀጥል እንደሚችል በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምእራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የትንተና እና ትንበያ ባለሙያ አቶ መልካሙ በላይ ለአሚኮ ገልጸዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ እየተከሰተ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአየር ንብረት ለውጥ ሣቢያ በሚፈጠር የኤሊኖ ክስተት ምክንያት የሚመጣ ነው።
የኤሊኖ ክስተት የሰላማዊ ውቅያኖስ አኹናዊ የሙቀት መጠን ከመደበኛው በዜሮ ነጥብ አምስት እና ከዛ በላይ ሲጨምር በሚፈጠር ትነት አማካኝነት አውስትራሊያ ላይ ከፍተኛ ዝናብ ሲጥል ከአካባቢው ያለው እርጥበታማ አየር በነፋስ ተገፍቶ ከኤሲያ ከፍተኛ አካባቢዎች ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ከሚነፍስ ቀዝቃዛ አየር ጋር ተዋህዶ በሀገራችን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚፈጥር ክስተት መኾኑን የትንተና እና ትንበያ ባለሙያው አቶ መልካሙ በላይ አብራርተዋል።
ከዓመታት በፊት የኤሊኖ ክስተት በየአስሥር ዓመቱ እና ከዛም በላይ በኾነ የጊዜ ቆይታ ውስጥ ይከሰት እንደነበረ እና አኹን ላይ ደግሞ የዓለማችን የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ከ 2 እስከ 7 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚከሰት ገልጸዋል።
የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ክስተቱ እንደሚቀጥል የሚጠቁሙ በመሆናቸው የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይገባል ሲሉ ባለሙያው አሳስበዋል። በተለይ ደግሞ የቆላማ አካባቢዎች አሁን ላይ ጤፍ የሚደርስበት ወቅት በመሆኑ በአስቸኳይ መሰብሰብ ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።
በደጋ አካባቢዎች በስፋት የሚመረተው ስንዴ እና ገብስ በመሆኑ ዝናቡ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል። ዝናቡ በሕዳር እና ታህሳስ ከቀጠለ ጉዳት እንደሚያደርስ ባለሙያው አስጠንቅቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!