“ወጣቶችን በሙያ በማብቃትና ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራን ነው”የጎንደር ከተማ ሥራና ሥልጠና መምሪያ

24

ጎንደር: ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ1 ሺህ 480 በላይ ወጣቶችን የሥራ ላይ ሥልጠና እየሠጠ ይገኛል።

ሥልጠናው በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙትን ሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ለመቀነሥ ወጣቶችን በሙያ በማብቃትና ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የታሠበ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው ኀላፊ ላቂያው አንዳርጌ ባለፉት አራት ወራት ከሠልጠኑ ወጣቶች መካከል 25 በመቶ የሚኾኑት በድርጅቶች ተቀጥረው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሠዋል።

ኀላፊው እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ሁሉም የሥራ ላይ ሥልጠና የወሠዱ ወጣቶች በድርጅቶች እንዲቀጠሩ ከሚመለከታቸው ጋር እየሠራን ነው ብለዋል።

ሥልጠናው የሕይወት ክህሎት፣ የሥራ አፈላለግ፣ አቻ ለአቻ እና መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀትን በተመለከተ መሠጠቱን የመምሪያው መረጃ ያመላክታል።

ሠልጣኞች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25፣ ከ12ኛ ክፍል በታች ያጠናቀቀ ወይም ያቋረጠ እና 60 በመቶ ሴቶች መኾናቸውን ኀላፊው አብራርተዋል።

ለሥልጠናው 65 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ሲሠራ መቆየቱን ያነሡት አቶ ላቂያው ገንዘቡ ለከተማው የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ የራሱ ድርሻ መኖሩን አንሥተዋል። በመኾኑም “የከተማውን ሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በግሉ ዘርፍ የሚሠማራ የሠለጠነ እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል” ነው ያሉት።

የዓለም ባንክ ፕሮጀክት ወደ ከተማው መምጣት ፋይዳው የጎላ መኾኑን የጠቀሡት የጎንደር ማተሚያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አማረ መስፍን ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሠማራት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል። ለሥልጠናው መሣካት ተቋማቸው 6 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በፕሮጀክቱ በተሠሩ ሥራዎች ጥንካሬያቸውን አዳብረው ፤ ክፍተቱን እና መፍትሔ አስቀምጦ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ለከተማውም ለውጥ መሥራት እንደሚገባ አንሥተዋል።

የጎንደር ከተማ ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት የ2015 ዓ.ም አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሔዷል።

ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም ዕትም
Next article“የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይገባል” የምእራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የትንተና እና ትንበያ ባለሙያ አቶ መልካሙ በላይ