
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአመጋገብ ሥርዓትን ለማሻሻል አኩሪ አተርን ወደ ምግብነት መቀየር የሚያስችል የተግባር ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል።
በአማራ ክልል ቆላማ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተመረቱ ከሚገኙ ምርቶች ውስጥ አኩሪ አተር አንዱ ነው። ሰብሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን በስፋት ይመረታል።
በ2014/15 የምርት ዘመን በክልሉ ከተመረተው አጠቃላይ የአኩሪ አተር ምርት 50 በመቶ የሚኾነው የተመረተው በዚሁ ዞን መኾኑን የዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጤናው ፈንታሁን ነግረውናል።
በ2015/16 የምርት ዘመንም የዞኑ አንዱ መለያ ምርት ተደርጎ በስፋት ማምረት መቻሉን ገልጸዋል። በምርት ዘመኑ 149 ሺህ 100 ሄክታር መሬት አኩሪ አተር ለማልማት ታቅዶ ከ135 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል። እስከ አሁን 48 ሺህ 400 ሄክታሩ ተሰብስቧል። እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል። ከዚህ በፊት ምርቱ እንደ ሌሎች ሰብል አኩሪ አተርን ለምግብነት የማዋል ልምድ ባለመኖሩ አምራቾችን የገበያ ችግር ያጋጥማቸው ነበር። ለኪሳራ ሲዳርጉ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ በ2016 ዓ.ም መግቢያ ላይ ጀምሮ የአኩሪ አተርን እሴት የመጨመር ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑ ተናግረዋል። “ትኩረት ያጣውን የአኩሪ አተር ምርት ለተለያዩ የምግብ አይነቶች እንዲውል በማድረግ ተፈላጊነቱን ጨምረናል” ነው ያሉት።
የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የማኅበረሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከአኩሪ አተር ምርት ወተት፣ ዳቦ፣ ቦምቦሊኖ፣ ሳንቡሳ፣ እንጀራ የመሳሰሉ ከ15 በላይ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ገዥ ያጣውን ምርት ዳግም ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል። የዞኑ ግብርና መምሪያም የምርምር ውጤቱን በመተማና ምዕራብ አርማጭኾ ወረዳዎች የማሥፋት ሥራ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
አቶ ጤናው እስካሁን በአስራ አንድ ቀበሌዎች ለሚኖሩ 1 ሺህ 700 ለሚኾኑ ነዋሪዎች ምርቱን ወደ ተለያዩ የምግብ አይነቶች በመቀየር የአመጋገብ ሥርዓትን ማሻሻል እንደሚቻል በተግባር የታገዘ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። በቀጣይም ተደራሽ ባልኾኑ ቀበሌዎች እና ሌሎች አምራች ወረዳዎች የማስፋት ሥራው ይቀጥላል ብለዋል።
ምክትል ኀላፊው እንዳሉት የምርምር ግኝቱ የአመጋገብ ሥርዓትን ከማሻሻል ባለፈ ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር ያገለግላል፤ የምርቱን ተፈላጊነት ይጨምራል፤ ያጋጠመውን የገበያ ችግርም ይፈታል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ የአምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!