
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብቃት ያለው ብዝኃነትንና አካታችነትን ታሳቢ ያደረገ ነፃና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንደሚገባ አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገልጸዋል።
እንደ አፈጉባኤው ገለጻ ነፃና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ማሻሻል ይገባል።
ለምክር ቤት አባላት “አገልጋይና ሥልጡን ሲቪል ሰርቪስ መገንባትና መምራት” በሚል ሃሳብ በዕለቱ ሥልጠና መሰጠቱም ተገልጿል።
ሲቪል ሰርቪሱን ወደፊት የሚያራምድ ረቂቅ ፖሊሲ የተዘጋጀና በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ከተወያዩበት በኋላ ፀድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጠቁመዋል። ተግባራዊ የሚደረገው የሲቪል ሰርቪስ ሀገራዊ ሪፎርሙን መሠረት ያደረገ እንደኾነም ተናግረዋል።
ለረቂቅ ፖሊሲውም ኾነ ለሪፎርሙ ተግባራዊነት የምክር ቤት አባላት ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ነው ያብራሩት።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ.ር) ባቀረቡት ሥልጠና በሀገሪቱ የነበረው ሲቪል ሰርቪስ ያልዘመነና የአገልግሎት አሰጣጡም ቅልጥፍና የሌለው እንደነበር ተናግረዋል። ከዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታና ከሀገሪቱ እድገት ጋር የማይጣጣም ኾኖ በመገኘቱ ከዓለማቀፍ እና ሀገራዊ እይታ በመነሳት ሲቪል ሰርቪሱን ማሻሻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመኾኑም ሲቪል ሰርቪሱን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱንና በቅርቡም ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግም ፍንጭ ሰጥተዋል።
ፓሊሲው ተግባራዊ ሲደረግ ብቃት ያለው፣ በሥነ-ምግባር የታነፀ፣ ሁሉን አካታች፣ ሲቪል ሰርቫንቱን በየጊዜው እየመዘነ ለተሻለ ደረጃና የደመወዝ ክፍያ የሚጋብዝ መኾኑንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የብቃትና የአቅም ውስንነት ለሚታይባቸው ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እየሰጠ የሚያበቃ መኾኑንም ነው ያመላከቱት። በተደጋጋሚ የአቅም ማጎልበቻ ተሰጥቶአቸው የማይበቁ ባለሙያዎች የሚኖሩ ከኾነ በሚመጥናቸው ሙያና ቦታ እንደሚመደቡም ነው ያብራሩት።
ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ.ር) ቀጣዩ ሲቪል ሰርቪስ የሚያስተናግደው ባለሙያ ብቃት ያለው፣ የሠለጠነ ስለሲቪል ሰርቪሱ በቂ ዕውቀት ያለው እና በሥነ-ምግባር የታነፀ መኾኑን ጠቁመዋል። ማንኛውም አካል ከወዲሁ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግም አሳስበዋል።
ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የሠራተኞች ቅጥርም በአንድ ማዕከል የሚካሄድ እና ከሰው እጅ ንክኪ ነፃና ብቃትን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነውም ብለዋል።
የሀገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ተሻሽሎ ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ በረቂቅ የሲቪል ሰርቪስ ፓሊሲው ላይ ከመወያየትና ረቂቁን ከማዳበር ጀምሮ ምክር ቤቱና የምክር ቤት አባላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!