“በፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ኾኗል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

53

ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያለው የቁጠባ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ማለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የባንኩ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ የኅብረተሰቡ የቁጠባ ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ለውጥ እየታየበት እንደሚገኝ ተናግረዋል። በመሆኑም ባንኮችን ጨምሮ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የቁጠባ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 19 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።

የቁጠባ መጠኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱንም አሳውቀዋል።

ሁሉን አቀፍ የቁጠባ ሥርዓት ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ሴቶች፣ አነስተኛና መካከለኛ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ጨምሮ ሌሎችም የቁጠባ ልምድ እንዲያዳብሩ ተደርጓል ብለዋል የባንኩ ምክትል ገዥ።

የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን በተለያዩ አማራጮች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የቁጠባና የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ተደርጓልም ነው ያሉት።

የዲጂታል ሥርዓቱ መስፋፋት፣ የአዳዲስ ባንኮች ወደ ሥራ መግባት፣ የካፒታል ገበያና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የመግባት እድል ተዳምረው ለቁጠባ ማደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆኑም አብራርተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም መስኮች የዲጅታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለክልሎች ሊሰራጭ ነው” የግብርና ሚኒስቴር
Next articleሲቪል ሰርቪሱን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሸጋገር የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱ ተገለጸ።