“የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለክልሎች ሊሰራጭ ነው” የግብርና ሚኒስቴር

77

ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለክልሎች ለማሰራጨት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በዘንድሮ ዓመት 300 ሺህ ሄክታር መሬት በኖራ ለማከም ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ የአፈር ሃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሊሬ አብዩ እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ ለክልሎች በማሰራጨት የአፈር አሲዳማነትን በቅንጅት ለመከላከል ጥረት ይደረጋል።

ሚኒስቴሩ የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ሰፊ ንቅናቄ እያካሄደ ነው ብለዋል አቶ ሊሬ። በዘንድሮው ዓመት 300 ሺህ ሄክታር አሲዳማ መሬት በኖራ ለማከም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልሎች በጠየቁት ሄክታር መሠረት የተሰላ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ኖራ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የኖራ ምርቱ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደሚሰራጭ ተናግረዋል።

አንድ ሄክታር አሲዳማ መሬት ለማከም በአማካይ 30 ኩንታል ኖራ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሊሬ የአንድ ኩንታል ኖራ ከምርት እስከ አርሶ አደሩ ማሳ እስኪቀርብ ድረስ 955 ብር ወጪ ይጠይቃል።

በበጀት ዓመቱ የታቀደው አሲዳማ መሬት ለማከም ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል ብለዋል።

የመንግሥት ኖራ ማምረቻ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ኖራ በቂ ባለመሆኑ ከግል ኖራ አምራች ፋብሪካዎች ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ሰባት ሚሊዮን የሚሆን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት ተጠቅቷል፤ ከዚህም ውስጥ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬቱ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን አስታውቀዋል።

በከፍተኛ ሁኔታ በአሲዳማነት ከተጠቃው ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካሁን ማከም የተቻለው 105 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከኖራ ሕክምናው በተጨማሪ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በማዘጋጀትና የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች በማልማት አሲዳማ መሬት ማከም እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በእንክብካቤ ጉድለት እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ የሚከሰት የአፈር ለምነትን ለመከላከል የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም እንደሚገባም አስረድተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሦስት ወራት ከ13 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝተናል” የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ
Next article“በፋይናንስ ተቋማት ያለው የቁጠባ ገንዘብ ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ ኾኗል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ