“በአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የአየር ትንበያ አገልግሎት ማዕከል እየተገነባ ነው” የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

34

ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ በአፍሪካ ቀዳሚ የኾነ የአየር ትንበያ አገልግሎት ማዕከል እየገነባ መኾኑን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ሦስት ባለ ዘጠኝ ወለል የአየር ትንበያ ማዕከል ሕንፃዎችን እየገነባ ነው ብለዋል። ለግንባታውም አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

እየተገነቡ የሚገኙት ዘመናዊ ሕንፃዎች ዘመኑ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና በአርቴፊሻል ኢንተለጄንስ (AI) የበለጸጉ መሣሪያዎች ይገጠምላቸዋል ብለዋል። ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የሳተላይት መረጃዎችን መጠቀም የሚያስችሉ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች በአየር ንብረት ላይ የተመሠረቱ በመኾናቸው መንግሥት ለአቪዬሽን፣ ለግብርና እና ለጤና ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት አቶ ፈጠነ። ኢንስቲትዩቱ አስተማማኝና ቀልጣፋ የአየር ትንበያ አገልግሎት ለመስጠት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሕንፃዎች በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ማዕከሉ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛው መሆኑን ገልጸዋል። የግንባታ ሂደቱም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

በሀገሪቱ አውቶማቲክ የአየር ትንበያ ጣቢያዎች እና የምልከታ ሥርዓቶች ተዘርግተዋል ያሉት አቶ ፈጠነ፤ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመኾን የአየር ትንበያ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍና ለማሻሻል የሚረዳ የሠለጠነ የሰው ኃይል ልማት ላይ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት ፡፡

እንደ አቶ ፈጠነ ገለጻ፤ ማዕከሉ የትምህርትና ማሠልጠኛ ክፍሎችን በማካተት በቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር ግንባር ቀደም እንዲኾን እየተሠራ ነው፡፡

«በተጨማሪም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የክልል የአየር ትንበያ አገልግሎት ማዕከላትን አቅም እያሳደግን ነው» ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ሕንፃዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ 18 ሺህ 800 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፉ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ 200 በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ናቸው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ግንባታው ሲካሄድ የቆየው ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን ሥራ ተቋራጮች እየተካሄደ መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመስዋእትነታችሁ ድል ፤በተጋድሏችሁ እድል አግኝተናል”
Next article“በሦስት ወራት ከ13 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝተናል” የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ