
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የዘመናት ሸክም የቀለለው እናንተ በከፈላችሁት መራር መስዋእትነት ነው፡፡ የተካዳችሁበት መንገድ ቢያም፤ የተጠቃችሁበት አግባብ ቢከብድም የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በእናንተ መከራ እና ስቃይ ነውና መቼም አትረሱም፡፡ ደማችሁ የማንነት መመለሻ፣ አጥንታችሁ የአማራ ሕዝብ ስብራት ወጌሻ ነውና ታሪክ በየዘመኑ ሲዘክራችሁ ይኖራል፡፡ በእናንተ ህልፈት በግፍ የሄደ ማንነት፤ በኀይል የተነጠቀ እርስት ተመልሷል፡፡
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ያንን ክስተት የሰሙት ደንግጠዋል፤ ያዩትን ማመን ተስኗቸዋል፡፡ ድርጊቱ ለዘመናት ከጸናው የኢትዮጵያዊያን እሴት ጋር ፈጽሞ ይቃረናል፡፡ ዓለም ሁሉ የሰማውን ለማመን ተቸግሯል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የወረደባቸው የድንጋጤ ናዳ ከትከሻቸው ሳይራገፍ ቀጣዮቹን ቀናት የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን ልሳን የሙጥኝ እንዲሉ አስገደዳቸው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ሃዘን ድባቡን አጥልቷል፡፡ የደርጊቱ ፈጻሚዎች በማፈር ፋንታ የሚወረውሩት ቃል የሰብዓዊነትን ቅስም ይሰብራል፡፡
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በቀበሮ ዋሻ የኖረ ወታደር እነርሱ “መብረቃዊ” ባሉት ጥቃት ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ እርቃኗን ቀርታለች፡፡ ክስተቱ አስፈሪ ብቻ ሳይኾን አሳፋሪም ነበር፡፡ አንገቱን ያልደፋ፤ በድርጊቱ ያልተከፋ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በሕይዎት የተረፉት ወታደሮች ተጋድሎ ኢትዮጵያዊያን “ላይክስ አይበድል” እንደሚሉት ኾኗል፡፡ በያሉበት ተሰባስበው በተበተኑበት ተጠራቅመው ያንን ክፉ ክስተት ቀልብሰው በድል ጎዳና ይመላለሳሉ ብሎ የሚያስብ ባይኖርም ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ናቸውና አድርገውታል፡፡
የድርጊቱ ፈጻሚዎች ከመሰል እኩይ ተግባራት እንደማይታቀቡ አደባባይ የዋለ ሃቅ ቢኾንም ፤ በዚህ ልክ ከሀገራዊ እሴት እና እምነት ይንሸራተታሉ ብሎ የጠበቀ ግን አልነበረም፡፡ ሰብል ሲሰበስብ የዋለን፤ አምበጣ ሲያባርር የደከመን ወታደር ትጥቁን ፈትቶ እንዳረፈ በወገኖቹ ጥቃት ይደርስበታል ብሎ ማመን ቀርቶ ማሰብ እንኳን ሳይከብድ አይቀርም፡፡ ጥንት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ከመኾናቸው የተነሳ ከጀርባ አይወጉም፤ ትጥቅ የፈታን አያጠቁም ነበር፡፡
ወታደር የሚለው ቃል በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለየ ከባድ ስሜት አለው፡፡ “ወጥቶ-አደር” ይሏቸዋል፤ የሀገራቸው ሉዓላዊነት እና የዜጎች ደኅንነት ከፈጣሪ በታች ተስፋ የሚደረገው በእነርሱ ላይ ስለኾነ፡፡ በየዘመኑ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ያገለግሉ ዘንድ ታሪክ እድል የሰጣቸው ወታደሮች ከጦር ሜዳ ጀብዱ ባለፈ አገልግሎታቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ገንብቶ የሚያስረክብ፣ የጤና ተቋም አዘጋጅቶ የሚሰጥ፣ አውራ ጎዳና ጠርጎ የሕዝብን ድካም የሚያቃልል እና የአርሶ አደሮችን አዝመራ ሰብስቦ ጎተራቸው ድረስ የሚያደርስ ወታደር ከኢትዮጵያ ውጭ ይኖራል ብሎ በድፍረት መናገር ይከብዳል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች በጦር ሜዳ አነጣጥሮ ተኳሽ ፣ ለችግር ጊዜ ደራሽ እና በሰላም ጊዜ አራሾች ናቸው፡፡ ለዛም ይመስላል ኢትዮጵያዊያን ከሰጋ ደማቸው ፤ ከአጥንት ነፍሳቸው ጋር ውትድርና የተቆራኘው፡፡
ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ እሳት፤ መሀሏ ገነት ኾኖ የዘለቀው በየዘመኑ ውድ መስዋዕትነትን በከፈሉ ወታደር ልጆቿ አጥንት እና ደም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ “የወታደር ልጅ ነኝ” የሚያኮራ እና የሚያስከብር ስም ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ወታደር እግር ጥሎት ከነመለዮው ከተማ ቢገባ እንኳ ማንም ቀና ብሎ ለማየት ይከብደዋል፡፡ ዛሬም ወታደር የኢትዮጵያን ፈተና የሚፈተን ፣ ከአቋሙ እና ከእምነቱ የማይንሸራተት የቃል ኪዳን ልጅ ኾኗል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ የማይወዛወዙ ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይጠራጠሩ ኾነው ቀጥለዋል፡፡ ብዙ ፈተና አለ፤ ብዙ ውጣ ውረድ አሁንም አልተዋቸው፤ ኢትዮጵያ ከችግሮቿ በላይ እንድትኾን ወታደር እንደ ፀጋ ተሰጥቷታል፡፡
በእናንተ ጽኑ ተጋድሎ የአማራ ሕዝብ የዘመናት የማንነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ዘመን ከፍቶ፤ ብልጠት ጠፍቶ ነገሮች የተዘበራረቁ ቢመስሉም መልክ እና ልክ ከመያዝ የዘለሉ ግን አይደሉም፡፡ የአማራ ሕዝብ የተገፋን ደግፎ የተጣላን አቅፎ ፤ የታረዘን አልብሶ የተራበን አጉርሶ ፈተናን የሚያሻግር ሕዝብ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ውለታ አይረሳም ፤ “በመስዋእትነታችሁ ድል ፤ በተጋድሏችሁ እድል አግኝተናል” ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉ ይዘክራችኋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!