
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እ.ኤ.አ ከ10 ዓመታት በፊት በ2013 ዓ.ም ነበር የተጀመረው፡፡ አገልግሎቱ አሁን ላይ ከ17 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት ወደ 190 ቢሊዮን የሚጠጋ የተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብም ችሏል፡፡ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ አገልግሎት ለደንበኞች ተደራሽ ማድረግ የቻለ እና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ አማራጭ የባንክ አገልግሎት ዘርፍም መኾን ችሏል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን እ.ኤ.አ በታኅሣሥ 2017 ነበር የጀመረው፡፡ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ‘‘አቢሲንያ አሚን’’ በሚል ሥያሜ የሸሪዓ መርሆዎችን መሠረት በማድረግ የተቀማጭ የብድር እና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ እየሠራም ይገኛል፡፡ አሁን ላይ ባንኩ በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲኾን በተቀማጭ የገንዘብ መጠንም 21 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡
አቶ ሙሐመድ ፈረጅ ከዚህ ቀደም የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በማስተዋወቅ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በማስታወቂያ ይዘት ዝግጅት፣ የድምፅ ንባብ ላይ እና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ለባለፉት 3 ዓመታት አብረው ሲሠሩ እንደቆዩ የአቢሲኒያ አሚን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልገሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡ በባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኩል ከተካሄዱ የመድረክ ዝግጅት እና ኘሮግራሞች መካከል ‘‘አሚን አዋርድ’’ በሚል ስያሜ የተዘጋጀውን የመጀመሪያውን ዙር የሥራ ፈጠራ ውድድር በማስተባበር፣ በመድረክ መሪነትና የሚዲያ ስርጭት ሥራን በብቃት ማከናወን እንደቻሉም ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ የሚጀመረውን የሁለተኛውን ዙር ‘‘የአሚን አዋርድ’’ የሥራ ፈጠራ ውድድር ዝግጅትን በአዲስ መንፈስ ከፍ ባለ ዝግጅት እና የኀላፊነት መንፈስ በመምራት አንባሳደርነታቸውን አንድ ብለው የሚጀምሩበት አጋጣሚ እንደሚኾን ይጠበቃል ብለዋል ምክትል ፕሬዝደንቱ ፡፡
ባንኩ ይህን ስምምነት ተከትሎም አምባሳደሩ ‘‘አቢሲንያ አሚን’’ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን በሚገባ በመረዳት አገልግሎቶችን በብቸኝነት በተለያዩ የሚዲያ ዘርፎች የማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ በድምፅ፣ በምስልና በጽሑፍ የተለያዩ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን በመጠቀም በውሉ ባንኩን ከክቡራን ደንበኞች ጋር የማስተዋወቅ ሥራውን የሚቀጥል ይኾናልም ብለዋል፡፡
አቶ ሙሐመድ ፈረጅ ከ15 ዓመታት በላይ በሚዲያ ባለሙያነት ፣በዜማና ግጥም ደራሲነት ፣በፊልምና ቲያትር ፣በድራማ ፣በማስታወቂያና በርካታ ታዳሚያን የተገኙባቸውን ታላላቅ መድረኮች በአጋፋሪነት እንዲሁም በጋዜጣና መጽሔት ውጤቶች አዘጋጅነት በቂ ልምድ ያካበቱ የማስታወቂያ እና ሚዲያ ባለሞያ ስለመኾናቸውም ተገልጿል፡፡ ባለሙያው ከተለያዩ የማስታወቂያ ድርጅቶች ጋር በማስታወቂያ ሀሳብ አመንጪነት፣ ተራኪነት እና ሌሎች ግብዓቶችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይም ይገኛሉ፡፡ ለዚህም አበርክቷቸው ከፍተኛ አድናቆትና ክብር በማኅበረሰቡ ዘንድ የተቸራቸው ስለመኾናቸም ምክትል ፕሬዝደንቱ ገልጸው አቢሲንያ ባንክም ለወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ አቶ ሙሐመድ ፈረጅን ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በይፋ አብስረዋል፡፡
ባንኩ በዘርፉ ላቀዳቸው በርካታ ውጥኖች የአቶ ሙሐመድ ሚና ወሳኝ እንደሚኾን ያለውን እምነት ገልጿል፡፡ በቀጣይ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጐት መሰረት ያደረገ ፈጣን እና አስተማማኝ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚሠሩ ሥራዎችን በሙሉ በልዩ ክትትል እና አትኩሮት የሚሠራባቸው ይኾናል ነው ያሉት፡፡ አቶ ሙሐመድ ፈረጅ በበኩላቸው “የሸሪዓን ሕጎችና የማኅበረሰቡን ዕሴት በሚያከብር ፣ለረጅም ጊዜ በአቢሲኒያ አሚን በኩል ጠንካራ ግንኙነት ከነበረኝ ባንክ ጋር በቅርበት በመሥራቴና አምባሳደር በመኾኔ ደስተኛ ነኝ ፤በሙያዬም የቻልኩትን ለማድረግ ቃል እገባለሁ” ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!