
👉ዩኒቨርሲቲው በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አድርጓል።
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ሰለሞን ፈንታው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ያደረገውን የእለት ምግብ ፣የሰውና እንስሳት መድኃኒት ድጋፍ ጃናሞራ ወረዳ ተገኝተው ማስረከባቸውን ገልጸዋል። አቶ ሰለሞን በወረዳው ችግሩ በተከሰተባቸው 13 ቀበሌዎች በተለይም ደግሞ ሕጻናት ፣እናቶች እና አረጋውያን ይበልጥ የችግሩ ሰለባ መኾናቸውን መመልከት እንደቻሉ ገልጸዋል። በአተት እና ትክትክ በሽታ የሰው ሕይዎት ጠፍቷል ብለዋል። የመጠጥ ውኃ ችግርም ሌላው ፈተና መኾኑን ገልጸዋል።
እንስሳት በድርቅ ምክንያት በመክሳታቸው ገበያ አውጥቶ ለመሸጥ እንኳ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በአብዛኛው ትምህር ቤት አልተገኙም ፤የተገኙትም የተሟላ የመማሪያ ቁሳቁስ የያዙ አለመኾናቸውን ገልጸዋል። ያጋጠመው ችግር የዛሬ ዓመት ምርት አምርተው እስኪጠቀሙ ዘላቂ በመኾኑ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አኹን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አውቆ መፍትሄ እንዲያገኝ ለማስቻል ጥናት እያካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ተቋማት በአጭር ጊዜ የሚደርሱ እና ድርቅን ሊቋቋሙ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን መምረጥ እና ማላመድ ይገባቸዋልም ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ለጊዜውም ቢኾን በሰሜን ጎንደር ዞን በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች 600 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ እህልና መድኃኒት ድጋፍ አድርጓል።
ለዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞንም 340 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ በቅርቡ ለተጠቃሚዎች ይደርሳል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!