“የሕዝብ ጥያቄዎች በሕግ ማዕቀፍ እንዲመለሱ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው” አቶ ሲሳይ ዳምጤ

78

ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች እና በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦችን ወስዶ መሥራት ከመሪዎች ይጠበቃል ብለዋል።

የተጀመረው የሰላም ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ገልጸዋል። የባሕር ዳር ከተማ ሰላም የበለጠ አሥተማማኝ እንዲኾን መሥራት ያሥፈልጋልም ነው ያሉት።

በከተማዋ የተጀመሩ እና በተለያየ ምክንያት የቆሙ የልማት ሥራዎችን ማሥቀጠል ይገባል ነው ያሉት። ልማት በራሱ ሰላም ያመጣል ያሉት ኀላፊው ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ መኾን አለባቸው፤ ኢንዱስትሪዎችም ሊስፋፉ ይገባል ብለዋል።

ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የሕዝብ ሚና መተኪያ እንደሌለውም ገልጸዋል። ያለ ሰላም እና ልማት ተጨማሪ ጥያቄዎችን መፍጠር ይቻል ካልሆነ በሥተቀር ጥያቄዎችን መፍታት እንደማይቻልም አመላክተዋል። በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ እየተግባባን፤ በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ እየተወያየን ችግሮችን መፍታት ይገባናል ነው ያሉት።

ጥያቄዎቻችንን በውይይት እና በንግግር መፍታት ካልቻልን የጀመርናቸው የልማት ሥራዎች ወደኋላ ይመለሳሉም ብለዋል። የቆዩ ችግሮችን በሥክነት በመለየት ጠንካራ ጉዳዮችን በማጠናከር ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ክልሉ ባለፉት ዓመታት በተረጋጋ ሁኔታ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የልማት ሥራዎችን መሥራት በማይችልበት ሂደት ውስጥ ማለፉንም ተናግረዋል።

ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን በሥክነት እና በማሥተዋል መመለስ ይገባልም ብለዋል። በሥሜት መናጥ ችግሮችን ለመፍታት አዳጋች ይኾናል ነው ያሉት።

በከተማዋ የሚሥተዋሉ የአገልገሎት አሠጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባሕር ዳርን የሚመጥን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን መፍጠር ካልተቻለ ወንበር ላይ መቀመጥ ትርጉም እንደሌለው ተናግረዋል። ለባሕር ዳር የሚመጥን መሪ ለመፍጠር እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ባሕር ዳር ሰላም ኾና እንድትቀጥል እየሠራችሁት ያላችሁትን መልካም ሥራ አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል ብለዋል። በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በፖለቲካ መሪዎች፣ በጸጥታ ኃይሎች እና በሕዝቡ የጋራ ጥረት ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የተረጋገጠ ሰላም እንዲኖር የሕዝቡ ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሚያዋጣው መወያየት፣ መደጋገፍ እና መመካከር መኾኑንም አንሥተዋል። ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ፣ የክልሉ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት በአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ዙሪያ አንድ ዓይነት አቋም እንደላቸውም ተናግረዋል።

በአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚደራደር መሪ አለመኖሩንም አሥታውቀዋል። በአማራ ክልል መንግሥት የሚመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ኾኖ በፌዴራል መንግሥት እና በኢትዮጵያውያን እገዛ የሚፈቱ ጥያቄዎች እንዳሉም መረዳት ይገባል ብለዋል። “የሕዝብ ጥያቄዎች በሕግ ማዕቀፍ እንዲመለሱ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው” ብለዋል።

በውዠንብር እና በኹከት ጥያቄዎችን መመለስ እንደማይቻልም ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረው ችግር ሰላማዊ በኾነ መንገድ መፈታት ይገባዋልም ብለዋል። ለአማራ ሕዝብ እና መንግሥት ጦርነት እንደማይጠቅመውም ገልጸዋል።

ሃሳብ ያላቸው መሪዎችን በመደገፍና በጋራ በመሥራት ክልሉን ተወዳደሪ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። መንግሥት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በሩ ክፍት መኾኑንም አመላክተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ክብር መጠበቅ፤ የከፈለውን መስዋዕትነት ማሥታወስ እንደሚገባም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ወርዶ መኖር እንደማይችልም ተናግረዋል።

የተጀመረውን ሰላም ማረጋገጥ፣ ማጽናት እና የሕዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። ሰላም ከተረጋገጠ የኑሮ ውድነቱን ማስተካከል እና መታገል እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመዲና ኢሳ በዓለም ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ምርጥ አትሌት ምርጫ ፍጻሜ ደረሰች።
Next article“ጥቅምት 24 መቼም የትም አይደገምም” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት