“የሕዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እንዲቻል ሰክኖ ማሰብ፣ እድል መስጠት እና በአንድነት መቆም ይገባል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

59

ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ ሁኔታዎችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይተል። ውይይቱን የመሩት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እንደማይመጣ ገልጸዋል። በሰላም እጦት ያጣናቸውን በማስታወስ ለሰላም መረጋገጥ መሥራት ይገባናል ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የሰላም ባለቤት መኾን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ከንቲባው ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባውም አመላክተዋል። በከተማዋ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ የነዋሪዎች ማንነት ማወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሁሉም ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ ከቻለ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎችን መምከር እና መገሰጽ ይገባዋልም ብለዋል። መንግሥት ጥያቄዎቹ እንዲፈቱ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉ መሪዎች የሕዝብ ጥያቄዎችን እንደማይረዱና እንደማይፈቱ አድርጎ መቁጠር ተገቢ አለመኾኑን ገልጸዋል። የአማራ መሪዎችን በመውቀስና በማጥላላት የሚፈታ ችግር አለመኖሩንም ተናግረዋል። “የሕዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እንዲቻል ሰክኖ ማሰብ፣ እድል መስጠት እና በአንድነት መቆም ይገባል” ነው ያሉት

ከመሪዎች ጋር መቆም የሚችል ሕዝብ ካለ ጀግና መሪ መፍጠር ይቻላልም ብለዋል። መሪን እንድንጠላ የሚያደረግ አስተሳሰብ እንድናሰርጽ ተሠርቶብናል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰከን ብሎ በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በሰከነ መንገድ የሕዝብ ጥያቄዎችን መፍታት እንዲቻል እድል መስጠት ይገባልም ብለዋል። የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች በጦርነት መፍታት እንደማይቻልም ገልጸዋል።

የሕዝብ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል እንዲፈቱ መንግሥት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ውስጣችንን መመልከት ይገባልም ብለዋል።

በከተማዋ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታ ማካሄድ እንደማይቻልም አሳስበዋል። ሕገ ወጥ ግንባት እንዳይኖር መሥራት ይገባል፣ ከተሠራም እናፈርሳለን ብለዋል። ሕገ ወጥ ግንባታ ገንብቶ የሚቀጥል አንደማይኖርም አስታውቀዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በሕጋዊ መንገድ የቤት ባለቤት እንዲኾኑ እንሠራለንም ብለዋል። መሬት ሊሰጥ ነው እያሉ በሕገ ወጥ መንገድ ሀብት የሚሰበስቡና ሕዝብን የሚያታልሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች ቦታ መስጠት በሚችልበት ጊዜ ለሕዝብ ግልጽ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ያለ አግባብ የቤት ኪራይ የሚጨምሩና ካልጨመርክ ውጣ በሚሉ አከራዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱም አስታውቀዋል። የሕዝብ ጥያቄዎችን በስክነት ለመመለስ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ፕሮጄክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ከንቲባው አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የመማር ማስተማር ሥራውን ጎድቶታል” የአማራ ክልል ምክር ቤት
Next articleመዲና ኢሳ በዓለም ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ምርጥ አትሌት ምርጫ ፍጻሜ ደረሰች።