
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ምልከታ አካሂዷል። በምልከታውም ተማሪዎችን በማግኘት የመማር ማስተማር ሂደቱ ምን እንደሚመስል ጠይቋል።
ተማሪ ፍቃዱ ምህረት የጠይማ የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ተማሪ ፈቃዱ ትምህርት በሰዓቱ ተጀምሯል፤ ከመጽሐፍት ውጭ ያሉ የትምህርት ቁሳቁሶች ተሟልተዋልም ብሏል።
የመማሪያ መጽሐፍ አለመኖር ግን ትምህርቱን ለመከታተል እንዳስቸገረው ገልጿል። ከመምህራን በሚሰጠው መረጃ ብቻ እየተማረ እንዳለ ነው የተናገረው።
የሽንብጥ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ አበቡ መዝገብም ከመጻሕፍት ችግር ውጭ ትምህርቱቷን በጥሩ ኹኔታ እየተከታተለች እንደምትገኝ ገልጻለች።
የሽምብጥ የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ጋሻው ጥሩነህ ከታቀደው በላይ ተማሪዎች ቢመዘገቡም የመጽሐፍ እጥረት መማር ማስተማሩን እየፈተነው መኾኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቱም ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ 3 ሺህ 576 ተማሪዎች ተመዝግበው እየተማሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ ሰርኬ ገዛኸኝ የመጽሐፍ እጥረቱ የሁሉም ትምህርት ቤቶች ችግር ነው ብለዋል። አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በመጀመሩ እና የታተሙ መጻሕፍት ትምህርት ቤቶች ላይ መግባት ባለመቻላቸው ለተማሪዎች መጽሐፍ አንድ ለአንድ ማድረስ አለመቻሉን ነው ያነሱት።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ በትምህርት ቤቶች የተደረገው ጉብኝት የትምህርት ቤቶችን ችግር ለማወቅ እና መፍትሔ ለማመላከት ይረዳል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን በአግባቡ የሠሩ በመኾኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣታቸውንም አረጋግጠናል ብለዋል። በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርት እንደተጀመረ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዊ የምክር ቤት አባላት በተመለከቷቸው ትምርት ቤቶች የተሻለ የቅበላ አፈጻጸም መኖሩን ተመልክተናል ብለዋል። ለተማሪዎች በቂ የመማሪያ መጽሐፍ አለመኖሩ ግን የመማር ማስተማር ሥራውን እየጎዳ መኾኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ችግሩ በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ የተፈጠረ ቢኾንም ትምህርት ቤቶች አቅማቸው በፈቀደ መጠን በሶፍት ኮፒ በማባዛት የትምህርት ሥራውን ማስኬዳቸው የሚበረታታ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሰላም እጦት ችግር በገጠመ ጊዜ መጽሐፍትን ከቦታ ወደ ቦታ ለማዘዋወር እንዲሁም የትምህርት ሥራውን ተዘዋውሮ ለመደገፍ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል። “በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የመማር ማስተማር ሥራውን ጎድቶታል” ሲሉም ተናግረዋል።
ሰብሳቢዋ “የትምህርት ሥራን አጠናክሮ ያልቀጠለ ማኅበረሰብ ተወዳዳሪ ልጆችን ለማፍራት ይቸገራል” ብለዋል። በመኾኑም የትምህርት ሥራው ከእንቅፋቶች የጸዳ እንዲኾን ለማስቻል ሁሉም ለሰላም መስፈን በጋራ መቆም አለበት ሲሉ አሰገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!