“የሕዝብ ጥያቄዎችን ፈጥኖ በመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ ክፍተቶችን መዝጋት ይገባል” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

37

ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ ኹኔታና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው። በከተማዋ ያለውን አሁናዊ ኹኔታ እና በቀጣይ መሠራት የሚገባቸው ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እየተደረገባቸው ነው። በውይይቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ አጥነት ችግር የሰላም እጦት ምክንያት እየኾነ መኾኑን ገልጸዋል። ወጣቶችን በሥራ መጥመድና የራሳቸውን ሃብት እንዲያፈሩ ማድረግ ለግጭት ጊዜ እንዳይኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት። በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሕዝብን በልማት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ካልተሠሩ ለውጥ ማምጣት አንችልም ብለዋል። ባለሃብቶች ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችሉ የልማት ሥራዎች ላይ መሠማራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

እውነተኛ ኾነው ለሕዝብ ልማት ከሚሠሩት የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ይልቅ ከሚያማው ጋር የሚያሙና የሕዝብን ጥያቄ የማይመልሱ መበርከታቸውንም አንስተዋል። የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ለኅዝብ ልማት በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባም ነዋሪዎች አንስተዋል።

በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፤ ከሕዝብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ጥያቄዎችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። በመጀመሪያ ደረጃ በሕዝብና በመሪዎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር መሥራት ይገባልም ብለዋል። የአማራ ክልል መሪዎች ከዓመታት በፊት ጀምሮ በሕዝብ ዘንድ እንዳይታመኑ ተሠርቶባቸዋል፣ መሪዎች በሕዝብ ዘንድ ታማኝ የሚያደርጋቸውን ሥራዎች መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የሕዝብ ጥያቄዎችን ሌሎች በመንጠቅ ለፓለቲካ መጠቀሚያ እያደረጓቸው ስለመኾኑም በውይይቱ ላይ ተነስቷል። “የሕዝብ ጥያቄዎችን ፈጥኖ በመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ ክፍተቶችን መዝጋት ይገባል” ሲሉ ነው ነዋሪዎች የተናገሩት። መሪን በየጊዜው ከመቀያየር ይልቅ ከሕዝብ ጋር በመተማመን ጠንካራ ሥራ መሥራት ለሰላም እና ለልማት እንደሚበጅም አንስተዋል። ግጭት የሚያስነሱ ምክንያቶችን ለይቶ በማውጣት ለሰላም መሥራት እንደሚገባም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ነዋሪዎች ሕዝቡን ወደ ውዥንብር የሚያስገቡ መረጃዎችን ማጥራትና መመከት እንደሚገባም አመላክተዋል። የመንገዶች መዘጋጋት የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው መኾኑንም ገልጸዋል።

“ሰላም ሲደፈርስ እና የሕግ የበላይነት ሲላላ ቀዳሚው ችግር እያረፈ ያለው በሕዝብ ላይ ነው” ብለዋል። የሕዝብን ኑሮ ስቃይ ውስጥ የሚከትቱ ጉዳዮችን ማርገብ እንደሚገባም ገልጸዋል። የሰላም ጉዳይ ለነገ የማይባል ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የደረሰው ውድመት ሳይካካስ ለሌላ ግጭትና ሕዝብን ለስቃይ መዳረግ እንደማይገባም ገልጸዋል። የሀገርና የሰላም ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለም፤ ሀሰተኞችን መታገልና ሰላምን በጋራ ማጽናት ይገባል ነው ያሉት።
ለሕዝብ ሰላም የሚሠራ መሪ መፍጠር ይገባልም ብለዋል። ሕዝብና መንግሥትን የሚያጋጭ መጠየቅ አለበት፤ ሀገር በሕግና በሥርዓት እንጂ በደላሎች መመራት የለባትም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

በከተማዋ በጦር መሳሪያ የታገዘ ቅሚያና ዘረፋ እየተስፋፋ መኾኑንም አንስተዋል። ነዋሪዎች ሰላም እንፈልጋለንም ብለዋል። በሀሰተኛ መረጃ ሀገር እና ሕዝብ ችግር ውስጥ እየገቡ ስለመኾኑም አንስተዋል። “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ሕዝብን ማጋጨት ሀገር የመሸጥን ያህል ነውር ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

መሪዎች ተከታታይና እውነተኛ መረጃዎችን በመስጠት ሕዝብን ከሀሰተኛ መረጃዎች ማዳን እንደሚገባቸውም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ ለዓመታት በማንነቱ ተነጥሎ መበደሉና ጥያቄው በፍጥነት አለመመለሱ ለችግሮች መነሻ ምክንያት ኾኗልም ብለዋል። የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው ብቻ መገደል፣ መፈናቀልና ተረጋግተው እንዳይኖሩ መደረጋቸው ሕዝቡን እንዲማረር እንዳደረገውም አስረድተዋል።

በሕግ ማስከበር ዙሪያ የሚስተዋሉ የሕግ መጣስ አካሄዶች ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል። የሕግ ማስከበር ሥራው በሕጋዊ መንገድ ብቻ መሠራት እንደሚገባውም አመላክተዋል። ለግጭት መነሻ የማይኾኑ ችግሮችን አጀንዳ አድርጎ ማንሳት የተገባ አይደለም፤ ትክክለኛ አጀንዳዎችን ግን በቁርጠኝነት መሥራት ይገባልም ብለዋል።

መሪዎች ለሰላም ቆራጥ የኾነ አመራር መስጠት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን መከላከል ከከተማ አሥተዳደሩ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ በስክነት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ከፖለቲካ መሪዎች በተጨማሪ የጸጥታ ኀይሎችም ከሕዝብ ጋር ጥልቅ ውይይት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ሁልጊዜ በተመሳሳይ ጥያቄ መቸገር እንደማይገባውና ጥያቄዎችን በአስቸኳይ በመፍታት ወደ ልማት መመለስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ሀገር በምክክር እና በውይይት እንደምትጸናም አስገንዝበዋል። እየተገዳደልን ያለነው እርስ በእርሳችን እንጂ የገባብን ጠላት የለም፤ ስለዚህ ችግሮቻችንን በውይይት ይፈቱልን ሲሉም ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርዋንዳ ለሁሉም አፍሪካውያን ከቪዛ ነፃ የጉዞ ፈቃድ ይፋ አደረገች።
Next article“በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የመማር ማስተማር ሥራውን ጎድቶታል” የአማራ ክልል ምክር ቤት