
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙት የአማራ ክልል ክለቦች ፋሲል ከነማ እና ባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ኾኗል፡፡
የሁለቱን ክለቦች ድህረ ጨዋታዎች ስንመለከት ዐጼዎቹ በተደራጀ ያጨዋወት ስልት ማሸነፍ እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 0 የረቱበትን ጨዋታ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚህ ጨዋታ በተለይ አማኑኤል ገብረሚካኤል አዘናግቶ በፍጥነት በማጥቃት ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡
በሌላ በኩል የጣና ሞገድ አጥቂዎች በፈጣን አጨዋወት በ35 ደቂቃ ውስጥ 3 ግቦችን በወልቂጤ ከተማ የግብ መረብ ላይ ያዘነቡበት ጨዋታ በጥንካሬ የሚነሳ ነው።
በፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ሀት-ትሪክ የሠራው ተጫዋችም የሚገኘው በዚሁ በባሕር ዳር ከተማ ክለብ ውስጥ መኾኑ የጨዋታውን ክብደት ያሳያል፡፡
ሴኔጋላዊው የጣና ሞገድ ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶም የብረት አጥርነቱ የዋዛ አይደለም፡፡ የተቃራኒ ተጫዋቾችን እንቅስቃሴ በንስር ዐይን ይከታተላል። ተጫዋቹ በዘንደሮው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የፍጹም ቅጣት ምትም ሳይቀር አድኗል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ባሳዩት ጠንካራ ወቅታዊ አቋም የዛሬውን ጨዋታ የበለጠ ተጠባቂ ያደርገዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን አራት ጨዋታዎች አድርጓል፡፡ ሁለቱ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንዱን ደግሞ ተሸንፏል፡፡ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል፡፡ የጣና ሞገዶቹ በሰባት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፋሲል ከነማ ከአራቱ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፏል፡፡ በሁለቱ ደግሞ አቻ ወጥቷል፤ ስለኾነም በስምንት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በ2015 የውድድር ዓመት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ባሕር ዳር ከተማ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ምሽቱ 12 ሰዓትም ሲቀጥል ወላይታ ድቻን ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኛል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!