
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚታረሰው ለም መሬት በከፍተኛ ኹኔታ በአፈር አሲዳማነት እየተፈተነ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። አማራ ክልል ከሀገሪቱ አጠቃላይ የእርሻ መሬት ውስጥ 39 በመቶ ገደማ፣ ከሀገራዊ ምርቱ ደግሞ 33 በመቶውን እንደሚሸፍን የግብርና ቢሮ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቸው ክልሉ በእርሻ እና በምርታማነት ሽፋኑ በሀገሪቱ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ቢኾንም በአፈር አሲዳማነት እየተፈተነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባለሙያው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህንን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት በኖራ የማከም ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በችግሩ አሳሳቢነት ልክ ትኩረት ባለመሠጠቱ የአፈር አሲዳማነት እየተባባሠ ነው ብለዋል። የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው የኖራ አቅርቦትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሠ መምጣቱ ነው የተናገሩት፡፡
ባለሙያው እንዳሉት በ2015 ዓ.ም ለኖራ ግዥ ከተጠየቀው 250 ሚሊዮን ብር የተመደበው 7 ሚሊዮን ብር ብቻ ወጭ ተደርጓል፡፡ ለመጠቀም ከታቀደው 300 ሺህ ኩንታል ኖራ ውስጥ 24 ሺህ ኩንታል ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ለማከም ከታቀደው 16 ሺህ 250 ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ማከም ተችሏል። የችግሩን አሳሳቢነት በተደጋጋሚ ለክልሉ የሥራ ኀላፊዎች በማቅረብ ትኩረት እንዲያገኝ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
በ2016 ዓ.ም የችግሩ አሳሳቢነት በፌዴራል ደረጃ ትኩት ማግኘቱን ያነሱት ባለሙያው ክልሉም ከ89 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማከም ታቅዷል። ለዚህ ደግሞ በሄክታር 30 ኩንታል ኖራ ለመጠቀም የሚውል የ2 ቢሊዮን ብር በጀት ጥያቄ ቀርቧል።
ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚመከረው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መጠን በላይ በመጠቀም የማምረት ሥራ እየተሠራ መቆየቱን ባለሙያው ያነሳሉ፡፡ ይህም ለአሲዳማነት አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል።
በቀጣይ የአፈር አሲዳማነትን ችግር መፍታት የሕልውና ጉዳይ ተደርጎ ካልተያዘ የምርታማነቱ ጉዳይ አጠያያቂ እንደሚኾነ ገልጸዋል። በአማራ ክልል በዓባይ ሸለቆ አካባቢ አሲዳማ አፈርን ሊያክም የሚችል ከፍተኛ የኖራ ክምችት መኖሩን ባለሙያው ጠቁመዋል። ደጀን ላይ ሥራ የጀመረውን የኖራ ወፍጮ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት በማስገባት እና በመገንባት ላይ ያለውንም በፍጥነት በማጠናቀቅ እንዲሁም የመራቤቴን የኖራ ፋብሪካ ሥራ እንዲጀምር በማድረግ የኖራ አቅርቦት ማሟላት ይገባል ብለዋል።
ባለሙያው በአሲድ የተጠቃ መሬት በኖራ ከታከመ በኋላ ምርታማነቱ ከ15 ኩንታል በላይ ጭማሪ ማሳየት ይችላል ነው ያሉት። ይህም ሥራውን በዋናነት ለመሥራት አነሳሽ ጉዳይ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!