
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች በወቅታዊ ኹኔታና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው። በከተማዋ ያለውን አሁናዊ ኹኔታ እና በቀጣይ መሠራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ውይይት እየተደረገባቸው ነው።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሕዝብ ግንኙነት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ የከተማዋን ወቅታዊ ኹኔታና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል።
በማብራሪያቸውም በሕዝቡ ብስለት ፣ ስክነትና ሰላም ወዳድነት ሰላሙን ማስጠበቅ መቻሉን አመላክተዋል። ሕዝቡ ሰላሙን በራሱ አቅም የመጠበቅ አቅም እንዳለውም ያሳየበት እንደነበር ተገልጿል።
በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መሪዎችን እንደገና የማደራጀት ሥራ መሠራቱ እና በከተማዋም መሪዎችን እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራ መከናወኑንም አንስተዋል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው አንኳር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመግታትና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማስተካከል አዲስ የተዋቀረው መዋቅር እየሠራ ነው ተብሏል። በከተማዋ የብልጽግና ፓርቲ የመሪዎች ሥልጠና በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ማስተናገዱም ተመላክቷል።
ሕዝቡ ሥርዓት አክባሪና የሰላም ዘብ ነውም ተብሏል። በከተማዋ በሐሰተኛ መረጃዎች የሚደናገሩ መኖራቸውም ተነስቷል። በከተማዋ በተፈጠረው ሰላም የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውም ተገልጿል። ሕዝቡ እውነታውን እየለየ መታገልና ለሰላም ዘብ የመቆም ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበትም ተብሏል።
አጀንዳ ተቀባዮች ከመኾን በመውጣት እንደሚገባም ገልጸዋል። በከተማዋ ሰላሙን ከማጽናት ባለፈ መደበኛ የልማት ሥራዎች እየቀጠሉ መኾናቸውም ተነስቷል።
በከተማዋ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ፣ የጸጥታ መዋቅሩን ማጠናከር ፣ መደገፍና ሌሎች ሥራዎችን ማሠራት እንደሚጠይቅም ተነስቷል። በመንግሥት መዋቅር ብቻ ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣ በመረዳት ሕዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።
በከተማዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከር ፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን መሳብና የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል። ከተማዋን ምቹና በመሠረተ ልማት የተሟላች ማድረግ በቀጣይ ሊሠራ የሚገባው ሥራ እንደኾነ አንስተዋል። ግብር በወቅቱና በአግባቡ መክፈል ፣ የንግድና ገበያ ልማት ዘርፉን በማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለመከላከል በቀጣይ እንደሚሠራም ተገልጿል።
በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ኹኔታ እንደምክንያት በመጠቀም የሚስተዋለውን ሕገወጥ የመሬት ወረራ የመከላከል ሥራ በትኩረት ይሠራበታልም ተብሏል።
ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን መለየት ፣ ማደራጀትና እንዲፈጸሙ መከታተል የማይታለፍ የወቅቱ ተግባርም ነው ብለዋል። ሁሉንም ሥራዎች በሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባም ተገልጿል። ሕዝብ የተሳተፈበት ማንኛውም ሥራ ውጤታማ እንደሚኾንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!