
ባሕር ዳር: ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አስፈላጊውን የሰው ኃይል በማሟላት የጸረ ሙስና ትግሉን አጠናክሮ ለማቀጣጠል እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚቴ ገልጿል፡፡ ሀገራዊ የሙስና ትግሉን ለማጠናከር እና ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ ለመታገል ያመች ዘንድ ከሀገር አቀፍ ጀምሮ እስከ ክልሎች ሥራውን የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሥራ ኅብረተሰቡን ላላስፈላጊ ብዝበዛ የዳረጉ ጉዳዮችን በማጋለጥ እና ወደ ፍትሕ በማቅረብም ውጤት የተገኘበት ሥራ ተከናውኗል፡፡
እንደ አማራ ክልል በሂደቱ ላይ ኅብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ጥቆማዎችን እንዲሰጥ ሲደረግ ቆይቷል፡፡የተቋቋመው ኮሚቴም ጥቆማዎችን በመያዝ የማጣራት ሥራ ሠርቷል፡፡ የተወሰኑ ጉዳዮችን ምርመራቸው ተጠናቅቆ ወደ ሕግ አካላት መምራት ተችሏል፡፡
በአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እና በክልላዊው የጸረሙስና ኮሚቴ ጸሐፊ ሀብታሙ ሞገስ ከወቅታዊው ጉዳይ ጋር በተገናኘ የጸረ ሙስና ትግሉ እንደበፊቱ ግለቱን ጠብቆ በመሄድ በኩል ውስንነት አለበት ብለዋል፡፡
በክልላዊው የጸረ ሙስና ኮሚቴ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ አባላት መኖራቸውንም አንስተዋል። ይህን ክፍተት ለመሙላት በቅርብ ቀን አባላቱ ተሟልተው የጸረ ሙስና ትግሉን ለማቀጣጠል እንደ ክልል ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አረጋግጠዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የሙስና ወንጀሎችን ሲመለከት ጥቆማ የመሥጠት ኀላፊነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል። በክልሉ ውስጥ በተዘጋጁት የጥቆማ መስጫ አማራጮች ጥቆማዎችን እየሰጠ ወንጀለኞችን ማጋለጥ አለበት ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ከአሁን በፊት የሰጣቸው ጥቆማዎች አስተማሪና በትክክልም ወንጀል የተፈጸመባቸው ኾነው ስለመገኘታቸውም ተናግረዋል።
የክልላዊው የጸረሙስና ኮሚቴ አሥተባባሪ ከፌዴራሉ ጋር በቅንጅትም እንደሚሠራ የተናገሩት ኮሚሽነሩ እርስ በእርስ እየተደጋገፉ እና በጋራ ሥራው እየተገመገመ እየተሠራ እንደኾነ አረጋግጠዋል፡፡በቅርቡም ኮሚቴዎቹ ሥራዎችን ለመገምገም እና አጠናክሮ ለማስቀጠል ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ መቀመጡን አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ክልል በፍትሕ ቢሮ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልሉ ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ውስጥ የተዘጋጁ የጥቆማ መስጫ ሳጥኖች መኖራቸውንም ገልጸዋለ። ወደ ክልል መምጣት ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ በየቀበሌ እና ወረዳው ላይ የተቀመጡ የጥቆማ መሳጫ ሳጥኖች እና ሌሎች አማራጮች በመኖራቸው ማኅበረሰቡ ጥቆዎችን በመስጠት ለጸረ ሙስና ትግሉ ጉልበት እንዲኾኑም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!