ለክብራቸው መታሰቢያ፣ ለታሪካቸው መዘከሪያ”

92

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውላል፤ ከዘመን ዘመን ይሸጋገራል፤ በትውልድ ልብ ላይ ይጻፋል፤ በታሪክ ብራና ላይ ይደምቃል፤ በረቀቀ ቀለም ይቀለማል፡፡ አበው ስምን ሲገልጹት “ወድቆ የማይሰበር፣ ሞቶ የማይቀበር፣ አባቴ የሰጠኝ ወንበር” ይሉታል፡፡ መልካም ስም አይሞትም፤ አይታመም፤ አያረጅም፤ አይወድቅምና፡፡

ገናና ስም አላቸው፤ ታሪክ ከፍ አድርጎ የሚጠራቸው፣ ገናና ዝና ዓላቸው፡፡ ትውልድ ሁሉ የሚዘክርላቸው፤ የከበረ ጀግንነት አላቸው ጠላት ሁሉ የሚሰግድላቸው፡፡ የሚደነቅ ብልሃት ተችረዋል፡፡ ሀገራቸውን በፍቅር፤ በአንድትና በኢትዮጵያዊነት ጸኑ መንፈስ መርተዋል፣ በዘመናቸውም ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ቀርጸዋል፤ ዘመናትን የምትሻገር፣ ለማንም የማትበገር ሀገርም አስረክበዋል፡፡

ሀገር በታወሰች ቁጥር ይታወሳሉ፤ ታሪክ በተዘከረ ቁጥር ይዘከራሉ፤ ድል አድራጊነት በታሰበ ቁጥር ይታሰባሉ፤ ነጻነት በተነሳ ቁጥር ይነሳሉ፤ ስለ አንድነት በተነገረ ቁጥር ይጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያን አብዝተው ወደዷት፤ ለክብሯና ለማዕረጓ ደከሙላት፤ ነጻነቷን አስጠበቋት፤ በዓለም ፊት አስከበሯት፤ ቅኝ ገዢዎችን የምትቀጣ አደረጓት፤ የነጻነት ብርሃንን አጸኑባት፤ የጥቁሮች ኩራት፣ የአፍሪካውያን እመቤት አሰኟት፡፡

ቅኝ ገዢዎች ሰገዱላት፤ ኃያላን ነን ያሉ ሁሉ ተንበረከኩላት፤ ሊያስገብሯት መጥተው ትምራቸው፣ ለወሬ ነጋሪ ታስቀራቸው፣ ይቅርታዋን ሰጥታ ወደ ተወለዱባት ምድር ትመልሳቸው ዘንድ ተማጸኗት፡፡ በባርነት ውስጥ የኖሩ ሁሉ መመኪያችን፣ እናታችን አሏት፡፡ ከባርነት ጨለማ መውጫ ብርሃናቸው፣ ወደ ከፍታው መራመጃ መንገዳቸው አደረጓት፡፡

ኢትዮጵያ አይደረግም የተባለችውን አደረገች፤ አይታለፍም የተባለውን አለፈች፤ አይቻልም የተባለውን ቻለች፤ ወደቀች፤ ለቅኝ ገዢዎች እጇን ሰጠች ስትባል ቅኝ ገዢዎችን ድል መታች፡፡ የቅኝ ግዛት ጠንሳሾችን አሳፈረቻቸው፤ ኃያላን ነን ያሉትን አዋረደቻቸው፤ ኢትዮጵያ ኾይ ወዮላት፣ ታላቅ ክንድ ሊያርፍባት ነው ያሏትን ሁሉ አስደነገጠቻቸው፤ የመሸነፏን ዜና ለናፈቁት የድል አድራጊነቷን ዜና አበሰረቻቸው፤ የባርነት ዘመኗን ለመቁጠር ለጓጉት የማይገረሰስ፣ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነጻነቷን አሳየቻቸው፡፡ የመጥፏቷን፣ የመንበርከኳን፣ እጅ የመስጠቷን መልእክት ለመስማት ለቋመጡት ያንበረከከችበትን ገድል ላከችላቸው፡፡

የነኳትን ድል መትታቸው፣ የሞከሯትን ቀጥታ ክፉ ያሰቡባትን አስደነገጠቻቸው፤ ክፉ የሚመኙላትን አርበደበደችባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዘመናት የመንግሥትነት፣ የሥልጡንነት፣ የነጻነት፣ የአንድነት፣ የሃይማኖት እና የአይደፈሬነት ታሪኳ እልፍ አዕላፍ ታሪኮች አሏት፡፡ የእርሷ ታሪክ እጅግ የረዘመና የገዘፈ ነው፡፡ ቀደምት መዛግብት ስለ እርሷ ይዘክራሉ፤ ስለ እርሷ ኃያልነት ይመሰክራሉ፡፡

በገዘፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎላ ብሎ የሚነሳ አንድ የታሪክ አምድ አለ፡፡ የዓድዋ የድል ታሪክ፡፡ በዚህ የድል ታሪክ ውስጥ ደግሞ የንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ታሪክ ከፍ ብሎ ይነሳል፡፡ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ የመጣባቸውን ሀገር ወራሪ እና ነጻነት ደፋሪ ከባለቤታቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ኾነው በመምራት ድል መትተዋል፡፡ በዙሪያቸው ጀግና የኢትዮጵያ ልጆችን አሰልፈዋል፤ ከዳር ዳር ኢትዮጵያውያንን አንድ አድርገው፣ ለአንዲት ሀገር አሰባስበዋል፤ ለአንዲት ሀገር ዘምተውና አዝምተው ድል አድርገዋል፤ የነበረውን ነጻነት አጽንተዋል፤ ነጻነት እንዳይደፈር፣ ሀገር እንዳይወረር ለመጪው ዘመን ትውልድ የቃል ኪዳን ማሕተም አኑረዋል፡፡

አጼ ምኒልክ በዘመናቸው የገዘፉ ታሪኮችን ሠርተዋል፤ በሠሯቸው የገዘፉ ታሪኮችም ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ አኑረዋል፡፡ የግዛት አንድነትን በማጽናት፣ ኢትዮጵያን ከመዘኑ ጋር ለማዋደድ በርካታ አሻራዎችን አሳርፈዋል፡፡ በክብርና በሞገስም ሀገራቸውን አስተዳድረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ወደዋል፤ ኢትዮጵያን በጽኑ ፍቅር ጠብቀው አስጠብቀዋል፡፡

ሰው ያልፋል፤ የማያልፍ ታሪክ ግን ይጽፋል፡፡ ምኒልክ አያሌ ታሪኮችን ሠርተው ሰው ናቸውና አለፉ፡፡ የታላቁ ንጉሥ የሞታቸው ዘመንም ታኅሣሥ 3 1906ዓ.ም እንደኾነ ተክለጻዲቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡

ተክላ ጻዲቅ መኩሪያ በመጽሐፋቸው አጼ ምኒልክ በዘመናቸው ክፉውን በክፉ ሳይኾን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ፣ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ ሀገር የሚሰፋበትን፣ ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ እረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን፣ ከማሰብና ከመፈጸም አልተቆጠቡም፡፡ የአውሮፓን ኃይል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል ብለዋል፡፡

እኒህ ታላቅ ንጉሥ ባለፉ ጊዜ ለክብራቸው መታሰቢያ፣ ለታሪካቸው መዘከሪያ የሚኾን ሐውልት ይቆምላቸው ዘንድ ልጃቸው ንጉሠ ነገሥታት ዘውዲቱ አሰቡ፡፡ ያንም አደረጉ፡፡ የአባታቸውን ሐውልት አሠሩ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በተሰኘው የታሪክ መጻሕፋቸው የምኒልክን ሐውልት ያሠሩት ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ናቸው፤ ሐውልቱ የተሠራው ጀርመን ነው፤ የተሠራውም ከነሐስ ሲኾን የሠራውም ሐርቲል የተባለ ጀርመናዊ ነው ብለዋል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ በመዘናቸው የአባታቸውን ሐውልት ቢያሠሩም ለምርቃት ሳይደርሱ በሞት ተቀደሙ፡፡

ሐውልቱን የማስመረቅ እድል ለቀድሞው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፣ ለኋለኛው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኾነ፡፡ የታላቁ ንጉሥ ምኒልክ ሐውልት ተመርቆ የተከፈተው በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ እና በግርማዊት እቴጌ መነን የዘውድ በዓል ዋዜማ ነበር፡፡ ንጉሡ ዋዜማውን የታሪክ ማስታወሻ፣ ዕለቱ መንገሻ አደረጉት፡፡ ያም ቀን ጥቅምት 22 1923ዓ.ም ነበር፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ በተሰኘው መጽሐፋቸው “የታላቁ ንጉሠ ነገሥት የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት በመናገሻው በቅዲስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እንዲቆም አድርገን ሥራው ተጨርሶ ነበርና በዘውዱ በዓል ዋዜማ እንዲመረቅ ስለተወሰነ ለዘውድ በዓላችን የመጡት እንግዶች ሁሉ በዚያው እንዲገኙ ኾኖ በታላቅ ክብር ከመጡ በኋላ ለዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ያቆምንላቸው በሚገባ መኾኑ የሚያስረዳ ቃል በረዥሙ ተናግረን ስንጨርስ ሐውልቱ የተሸፈነበት መጋረጃ ሲገለጥና ሐውልቱ ሲታይ በኢትዮጵያውያን ልብ የተደረገው ደስታ ይኼን ያህል ነው ተብሎ ሊገመት አይችልም” ብለዋል፡፡

የእምዬ መታሰቢያ ሐውልት በሚወዱት፣ በሚመኩበት፣ ዓድዋ ድረስ ዘምቶ ድል ከእርሳቸው ጋር እንድትኾን አንዳረገላቸው በሚያምኑት በቅዱስ ጊዮርጉስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ቆመ፡፡ የሚዋደዱ አይለያዩምና፡፡ የሚዋደዱ ፍቅራቸው ዘላለማዊ ነውና ምኒልክ በሚወዱት ታቦት አጸድ ሥር ገዝፈው ቆሙ፡፡ በፈረሳቸው በአባ ዳኛው ላይ በክብር ተቀምጠው፣ ወደዚያች የድል ቦታ ፊታቸውን አዙረው በግርማ ይታያሉ፡፡

ብላታ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከ1922 እስከ 1927 በተሰኘው መጽሐፋቸው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሐውልቱ ምረቃት ቀን የተናገሩትን ሲጽፉ “የታላቁ ንጉሥ ዘዳግማዊ ምኒልክ የቆመበት ይሕ ቀን ለሙሉ ኢትዮጵያ ሕዝብ የደስታ ቀን መሆኑን ማንም አይዘነጋውም፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ድካሙ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ በሠራው ሥራ ለስሙ መልካም መታሰቢያ ትቶ ከመሄዱ በቀር ሌላ የሚበልጥ ነገር የለምና ዛሬ ይሕ ሐውልት መቆሙ አጼ ምኒልክ የድካማቸውን ዋጋ ለማግኘት የሚገባቸው እጅግ የታደሉ መሆናቸውን ያስረዳናል፡፡ …. ሰው ፍጡር ስለሆነ ከዚህ የበለጠ ለማድረግ አይችልምና ነው እንጂ አጼ ምኒልክ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የሠሩትን መልካም ሥራ ሁሉ ስናመዛዝነው ይህ ሐውልት ዋጋቸው ለመኾን አይበቃም፡፡…. ወደፊትም ለነገሥታት ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያ ትልልቅ ሥራ የሚሠሩና የሠሩ አርበኞች ለሥራቸውና ለስማቸው መታሰቢያ የሚኾን ሐውልት እያከታተልን እናቆማለን” ማለታቸውን ጽፈዋል፡፡

ሐውልቱ በተመረቀ ጊዜ እልልታው ቀለጠ፡፡ ሕዝብ ደስ አለው፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትናንትን እንደሚያከብሩ፣ ታሪክን እንደሚዘክሩ አሳዩ፡፡ ለነገም ታሪክ የሚሠራ እንደሚከበር አመላከቱ፡፡
ዓመታት አለፉ፡፡ በዓድዋ ተራራ ላይ ድል የተመታችው ኢጣልያ ለዳግም ወረራ መጣች፡፡ ለአዕምሮ የሚከብዱ ግፎችንም ፈጸመች፡፡ ግፍ እየፈጸመች በዙፋኑ መቀመጫ አዲስ አበባ ደረሰች፡፡ ኢጣልያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማድረግ እና የኢትዮጵያውያንን ሥነ ልቡና ለመስበር የሚመኩባቸውን፣ ለዘመናት የጠበቋቸውን ታሪኮቻቸውን፣ የአምልኮ ሥርዓት መፈጸሚያቸውን እየለየች ጥቃት ትፈጽም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ግፍ በበዛባቸው ቁጥር የሚጠነክሩ እና ለድል የሚነሱ ነበሩና ኢጣሊያ አልተሳካላትም፡፡ ሌላ ሽንፈት ይዛ ከጀግኖች ሀገር ወጣች እንጂ፡፡

በኢጣልያ ወረራ ወቅት ጉዳት ከደረሰባቸው ቅርሶች መካከል የምኒልክ ሐውልት አንደኛው ነበር፡፡ ጳውሎስ ኞኞ በታሪክ መጽሐፋቸው “ኢጣልያ አዲስ አበባን እንደያዘች ሐምሌ 4 ቀን 1928 ዓ.ም የምኒልክ ሐውልት ካለበት ቦታ ወርዶ ተቀብሮ ነበር፡፡ ነጻነት ከተመለሰ በኋላ ሐውልቱ ከተቀበረበት ወጥቶ እንደገና በድሮው ሁኔታ ቆመ፡፡ እንደገናም ሚያዚያ 27 1934ዓ.ም ተመረቀ” በማለት ጽፈዋል፡፡

በምኒልክ ሐውልት ግርጌ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሞያ አይደለም፡፡ ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሞያ ነው” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ጥቅምት 22/1923 ዓ.ም በመናገሻ ጊዮርጊስ ቤተክስቲያን አጠገብ የምኒልክ ሐውልት በክብር የቆመበት ነው፡፡ እርሳቸው ለታላቅ ታሪክ የተለወዱ፣ ታላቅ ታሪክ የሠሩ፣ የታላቅ ሀገር መሪ ታላቅ ሰው ናቸውና ክብር ይድረሳቸው፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ ዩጋንዳ አቀና።
Next article“ሰላማችንን ለማጽናት የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው