ከቅርጫት ኳስ ተጫዋችነት እስከ ዝነኛ የዓለም ዋንጫ ዳኛነት

42

ባሕር ዳር: ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተወለደችው እ.ኤ.አ በ1988 በሩዋንዳ ምዕራባዊ ግዛት ሩሲዚ በተባለ ከተማ ነው ፤ ሳሊማ ሙካንሳንጋ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት ዳኛ።

በትውልድ መንደሯ በበርካታ ሰዎች የቅርጫት ኳስ ጨዋታን ይዘወተራል ፤ በወቅቱ ሳሊማ ኳስ ታቀብል ነበር፡፡ ቀስ በቀስም ቅርጫት ኳስ መጫወትን ጀመረች፡፡ በታታሪነትም ጥሩ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ለመኾን በቅታለች፡፡

በታዳጊነቷም ለሩዋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመረጠች፡፡ ቅርጫት ኳስን በደንብ ብትጫወትም የምትዝናናው እግር ኳስን በመመልከት ነበር፡፡

ፍላጎቷን የተረዱት የስፖርት መምህሯ በአንድ አጋጣሚ የወንዶችን የእግርኳስ ግጥሚያን እንድትዳኝ እድሉን አመቻቹላት፡፡ ከአጋጣሚው በኃላ ሳሊማ ከቅርጫት ኳስ ተጫዋችነት የእግር ኳስ ዳኛ ለመኾን ፍላጎት አደረባት፡፡

ዝንባሌዋን የተረዱት የስፖርት ሳይንስ መምህሯ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እንዳለች የዳኝነት ትምህርት እንድትወስድ አደረጉ ።

ጎን ለጎን ትምህርቷ ላይ የበረታችው ሳሊማ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በነርስነት ተመረቀች፡፡ ነገር ግን ከራሷ ጋር ብዙ ከመከረች በኋላ በተማረችበት ዘርፍ ሳይኾን በእግር ኳስ ዳኝነት ለመቀጠል ወሰነች፡፡ እናም ወደ ሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀርባ የ”ልዳኝ” ጥያቄ አቀረበች፡፡

የሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በአማተር ደረጃ ጨዋታዎችን እንድትመራ ውሳኔውን አሳወቃት፡፡ለመጀመሪያ ጊዜም የወንዶች አማተር እግር ኳስ ጨዋታዎችን እና የሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታዎችን እንድትመራ ተደረገ፡፡

በዚህ መልኩ ሙያዋን አሳደገች ፤ ፌዴሬሽኑም የዳኛዋን ብቃት ካረጋገጠ በኋላ የሀገሪቱን አንደኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ እንድትመራ ወሰነ፡፡ እሷም ጨዋታዎችን በብቃት መርታብቃቷን አስመሰከረች፡፡

ቀስ በቀስም የዳኝነት ብቃቷ እንደ ቢቢሲ ባሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ተቋማት መወራት ቻለ፡፡

ሳሊማ ከስኬታ ጀርባ ፈተናዎችን አሳልፍለች ነገር ግን በዓለም ዙሪያ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ላሉ ልጃገረዶች ዓርዓያ ለመኾን ተስፋ በመሰነቋ ላጋጠማት ፈተና እጅ ሳትሰጥ ሥራዋን ቀጠለች፡፡

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር /ፊፉ/ በይፋዊ ገጹ እንደዘገበው የኳታሩን የዓለም ዋንጫ እንዲመሩ ከተመረጡት ሦስት ሴት ዳኞች አንዷ ለመኾን በቅታለች፡፡

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴት ዳኛ በመኾን ጨዋታዎችን በብቃት በመዳኘትም ራሷን ብቻ ሳይኾን መላ አፍሪካዊን አኩርታለች።

በ2022 በካሜሩን በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በመሀል ዳኝነት ጨዋታዎችን በብቃት በመምራትም አድናቆትን አትርፋለች ሳሚራ፡፡

ህልሟን በጥረቷ እየኖረች ያለችው ይቺ ዳኛ የኦሎምፒክን ፣ የሴቶች የዓለም ዋንጫን ፣ በአፍሪካ የሴቶች ዋንጫን እና በካፍ የሴቶች ሻምፒየንስ ሊግን በመምራት አንቱ የሚያስብል ታሪክ ባለቤት ናት አኹን ላይ።

የእንግሊዝ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) በ2022 ከመረጣቸው 100 ምርጥ የእግር ኳስ ዳኞች አንዷ ለመኾንም በቅታለች፡፡

“በተለይ የወንዶች የዓለም ዋንጫን መምራት በጣም አስደሳች ነው ፤ ለእኔ ይሄ ትልቅ የመብት እና የእኩልነት ምልክት ነው” ስትል ለፊፋ ዶትኮም ተናግራለች።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጸጥታ ችግር ምክንያት 310 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ኾነዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳሰበ።
Next articleየኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ ዩጋንዳ አቀና።